ቀጥታ፡

በምክክሩ ሁላችንም አሸንፈናል- ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ በጠብመንጃ ምንጊዜም ያሸነፈ ኃይል የለም፤ ሁላችንም አሸናፊ የሆንነው በምክክር ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

ኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ መርሐ ግብር በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የኢጋድ ዋና ጸኃፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር)፣ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬኒያታ፣ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴንጎን ኦባሳንጆ እንዲሁም የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በማጠቃለያ መርሃ ግብሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ በምክክሩ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ኢትዮጵያን አሸናፊ ላደረጉ ተመካካሪዎች ምስጋና አቅርበዋል።

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ቆይታችን እኛ ኢትዮጵያውያን መቀራረብና መፋቀር ምን ማለት እንደሆነ በተግባር አይተናል ብለዋል።

ምክክር ይጀመራል እንጂ በማግስቱ አያልቅም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ በምክክሩ የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች በቀጣይ የምክክር ባህል በየአከባቢው እንዲዳብር ትልቅ አቅም እንደሚሆኑ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ የምትሆነው በምክክር እንጂ በጠብመንጃ አይደለም ሲሉም ነው የተናገሩት።

ከዚህ አኳያ ሀገራዊ ምክክሩ ሁላችንም አሸናፊ አድርጎናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም