ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የአፍሪካ በራሷ እጣ ፈንታዋን የመወሰን ጉዞ ማሳያ ነው- ኡሁሩ ኬንያታ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2018 (ኢዜአ)፦ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የአፍሪካ በራሷ እጣ ፈንታዋን የመወሰን ጉዞ ማሳያ መሆኑን የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የመዝጊያ ስነ ስርዓት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በመካሄድ ላይ ነው።

የቀድሞ ኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ጉባኤው የአፍሪካ ራስን የመቻል ጉዞ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ መዲና ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ህያው ከተማ ናት ብለዋል።

አፍሪካ መፍትሄዎችን ስትፈልግ ዞር ብላ የምታየው ወደ አፍሪካ መዲና ሆነችው አዲስ አበባ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የቆዩ የታሪክ ቁርሾዎችን ለመፍታት ያዘጋጀው ጉባኤ ብዝሃ ድምጾች የተሰሙበትና ጉባኤው የሀገር ፍቅር ስሜት የተንጸባረቀበት መሆኑን አመልክተዋል።

ጉባኤው ከሁሉም የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት መሆኑ አካታች እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል።

በጉባኤው ላይ ለተሳተፉ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።

ኢትዮጵያ ታሪኳ የጽናት እና የአይበገሬነት ምልክት ናት ያሉት ኬንያታ የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።

የአድዋ ድል ለአፍሪካ ነጻነት ትግልና ነጻ መውጣት ትልቅ መሰረት የጣለ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ መስራች እንደሆነችና የአፍሪካ ህብረት ( የአፍሪካ አንድነት ድርጅት) መቀመጫ መሆኗን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫ ናት ብለዋል የቀድሞ የኬንያ ፕሬዝዳንት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም