ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው የእኛነት መንፈስን በማጎልበት ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ታሪካዊ ምዕራፍ ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 16/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ከልዩነትና ከ “እኔነት” ወደ “እኛነት” በመሻገር የጋራ ሀገራዊ እይታ የተገነባበትና ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወደ ማጠቃለያ ምዕራፍ ደርሷል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመካካሪዎች እንደተናገሩት፤በልዩነቶች ላይ ተቀምጦ በመወያየት ወደ የጋራ መግባባት መምጣት ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና የጋራ እድገት መሠረት የጣለ ነው።  

ከተመካካሪዎቹ መካከል ኢሴ ባኔ ሀጂ አቡበከር እንደገለጹት፤ ምክክሩ ችግሮችን በውይይትና በመግባባት መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ ነው።   

በምክክሩ የተለያዩ ሀሳቦች ቀርበው ወደ አንድ የጋራ ሀሳብ መምጣት መቻሉን ጠቁመው፤ ሁሉም ተሳታፊ ሀሳቡን በነፃነትና በእኩልነት የሚያቀርብበት አሠራር መኖሩን ገልጸዋል። 

ሀገራዊ ምክክሩ በሀገሪቷ ባህል ሆኖ መቀጠል ያለበት መሆኑንም ተናግረዋል።    

ምክክሩ ገለልተኛና አሳታፊ መድረክ በመሆኑ ሀሳባቸውን ያለገደብ ለማንሳት እድል እንዳገኙ የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ  በሀይሉ በልጅጋ ናቸው። 

በልዩነቶች ላይ ተቀምጦ መወያየት በራሱ ሀገራዊ ድል መሆኑን ገለፀው፤ በስምንቱም ዐበይት አጀንዳዎች ላይ ጥልቅ ውይይት መካሄዱን ጠቁመዋል። 

ምክክሩ ተሳታፊዎችን ከ“እኔነት” ወደ “እኛነት” በማሸጋገር ሀገራዊ እይታን እንዲያዳብሩ ማድረጉን አንስተው፤ ምክክሩ ጠንካራና በጋራ የምትቆም ኢትዮጵያ ያሸነፈችበት መሆኑን ገልጸዋል።   

ሌላኛው ተመካካሪ ቄስ ደነቀ ዳሪሞ በበኩላቸው፤ ሀገራዊ ምክክሩ ታሪካዊ ሂደት መሆኑን ገልጸዋል።

የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ዜጎች አንድ ኢትዮጵያ ሆነው ለሀገሪቷ የሚመች መፍትሔ ለመፈለግ መምከራቸውን አውስተዋል።

ሁሉም ተሳታፊዎች ሀሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸው ተጠብቆ በመወያየት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ችግሮችን በምክክር መፍታት ለወደፊቱ ትውልድ የሚጠቅም አዲስ ታሪክ መጻፉን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገሪቷ ዘላቂ ሰላም መስፈን ጉልህ አስተዋጽዖ የሚኖረው ሲሆን፤ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ተምሳሌት ሊሆን የሚችል ሂደት መሆኑን  አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም