ቀጥታ፡

ጉባኤው በኢትዮጵያ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማጠናከር ጉልህ ሚና አለው - ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ 76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ በኢትዮጵያ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለው የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

76ኛው የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ ቀጣናዊ ኮሚቴ ጉባኤ ከነሐሴ 18 - 22 ቀን 2018 ዓ.ም እንዲካሄድ ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ መመረጧ ይታወሳል።

በጉባኤው ከ47ቱ የዓለም ጤና ድርጅት የአፍሪካ አባል ሀገራት የተውጣጡ የጤና ሚኒስትሮችን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ የልማት አጋሮችን እንዲሁም የቀጣናውና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች መሪዎችን ጨምሮ ከ800 በላይ ተሳታፊዎች ይሳተፋሉ።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ጉባኤው በጤና ዘርፍ  በአምስት ምሰሶዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ይካሄዳል።

በአፍሪካ ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ስርዓት መገንባት፣ የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ክብካቤ፣ ዲጂታል የጤና ስርዓት መገንባት፣ የጤና ባለሙያዎች አቅም ግንባታና የሀገር ውሰጥ ምርቶችን ማሳደግ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ የእናቶችንና የህጻናትን ሞት መቀነስና የጤና አገልግሎት ማሻሻል እንዲሁም በሰለጠኑ ባለሙያዎች የቅድመ ወሊድ ክትትል ተጨባጭ ውጤቶች ተገኝተዋል ሲሉም ገልጸዋል።

በመሆኑም ጉባኤው በኢትዮጵያ በጤና እና በሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

በተጨማሪም ጉባኤው ለኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ፣ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎችም በርካታ ትሩፋቶች እንደሚኖረውም ጨምረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም