ቀጥታ፡

አካባቢን ከብክለት በመጠበቅ ጤናማና አምራች ዜጋን የማፍራቱ ተግባር ይጠናከራል

ገንዳውሃ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፡- ህብረተሰቡ አካባቢውን ከብክለት በመጠበቅና በማፅዳት ጤናማና አምራች ዜጋን የማፍራት ተግባርን አጠናክሮ እንዲቀጥል የምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ጽህፈት ቤት አስታወቀ። 

በገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር "ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ" በሚል መሪ ሐሳብ የተዘጋጀ የሀገራዊ እንቅስቃሴ አካል የሆነ የፅዳት ዘመቻ ዛሬ ተካሄዷል።


 

የምዕራብ ጎንደር ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ መልካም ዋሲሁን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ፅዱና ውብ አካባቢን መፍጠር ለጤናማ ማኅበረሰብ ግንባታ መሠረት ነው። 

አካባቢን ከፕላስቲክና ከሌሎች ደረቅ እንዲሁም ፈሳሽ ቆሻሻዎች ነፃ በማድረግ ፅዱ አካባቢን መፍጠር አምራች፣ ጤናማና ውጤታማ ትውልድ ለማፍራት ወሳኝ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል። 

ለዚህም ማኅበረሰቡ የአካባቢ ፅዳት ሥራን የአንድ ወቅት ዘመቻ ሳያደርግ የዘወትር ተግባርና የኑሮ ባህሉ በማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ጉርባ በበኩላቸው፣ ከአካባቢ ንፅህና ጉድለት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ሕብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንፅህና ዘወትር ሊጠብቅ ይገባል ብለዋል። 

አካባቢው ሞቃታማ በመሆኑ እንደ ወባ፣ ኮሌራና መሰል ተላላፊ በሽታዎች በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰቱ የግልና የአካባቢን ንፅህና መጠበቅ ባህል ሊደረግ ይገባል ነው ያሉት።

የገንዳውኃ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ አዳነ ሀሰን እንዳሉት፣ ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹና ለባለሀብቶች ሳቢ ለማድረግ በአካባቢ ንፅህና አጠባበቅ ላይ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል። 

የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የንግዱ ማኅበረሰብና የወጣት አደረጃጀቶች አካባቢያቸውን ሰላም ከመጠበቅ ጎን ለጎን ፅዱና ለኑሮ ተስማሚ ለማድረግ የጀመሩትን ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

"ለነገው ሀገር ተረካቢ ሕፃናት ፅዱ ከተማን ማስረከብ የእኛ የወጣቶች ኃላፊነት ነው" ያለው ደግሞ በፅዳት ዘመቻው የተሳተፈው ወጣት ሃብታሙ አክሊሉ ነው። 

ከተማዋን ከፕላስቲክና ከሌሎች መርዛማ ኬሚካሎች በማፅዳት ማራኪና ለነዋሪዎቿ የምትመች ተመራጭ ከተማ ለመፍጠር በሚደረገው ሂደት በቀጣይም የድርሻውን እንደሚወጣ አረጋግጧል።

በፅዳት ዘመቻው የከተማዋ የመንገድ ዳርቻዎች፣ የገበያ ስፍራዎችና የሕዝብ መዝናኛ አካባቢዎችን ከቆሻሻ ፅዱ የማድረግ ሥራ የተከናወነ ሲሆን፣ በየሳምንቱም የፅዳት ዘመቻው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ከወጣው መርሃ ግብር ለመረዳት ተችሏል።

በተካሄደው የፅዳት ዘመቻም የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የመንግሥት ሰራተኞች፣ የአካባቢው ነዋሪዎችና የተለያዩ አደረጃጀቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም