የሻደይ በዓል ፍቅርን፣ አንድነትንና ማኅበራዊ እሴትን የሚያጠናክር የሴቶች የነፃነት በዓል ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሻደይ በዓል ፍቅርን፣ አንድነትንና ማኅበራዊ እሴትን የሚያጠናክር የሴቶች የነፃነት በዓል ነው
ሰቆጣ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፡- የሻደይ በዓል ፍቅርን፣ አንድነትንና ማኅበራዊ እሴትን የሚያጠናክር የሴቶች የነፃነት በዓል በመሆኑ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሴቶች፣ ወጣቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገለጸ።
የሻደይ በዓል የሴቶች ነፃነት፣ ባህል ውበትና ማኅበራዊ ትስስር መገለጫ ከመሆኑም ባለፈ፣ ለሀገር ሰላምና ለዘላቂ ልማት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው።
በየዓመቱ በነሐሴ ወር አጋማሽ በሚከበረው በዚህ በዓል ሴቶችና ወጣቶች አደባባይ ወጥተው በነፃነት በመጫወት ፍቅርንና አንድነትን የሚያጎሉበት አውድ ይፈጠራል።
የሻደይ በዓል ከነፃነት ተምሳሌትነቱ ባለፈ ሴቶች ለልጆቻቸው ልምድ የሚያካፍሉበት ሥርዓት መሆኑም ይገለፃል።
መምሪያው በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ቀን ጀምሮ የሚከበረውን የሻደይ በዓልን ምክንያት በማድረግ የፓናል ውይይት አካሄዷል።
በወቅቱም የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ ትብርህ ታደሰ እንደገለጹት፣ የሻደይ በዓል ፍቅርን፣ አንድነትንና ማኅበራዊ እሴትን የሚያጠናክር የሴቶች የነፃነት በዓል በመሆኑ የጋራ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያስችላል።
ሻደይ የአንድነትና የትብብር እሴቶችን አጣምሮ የያዘ መሆኑን ገልጸው፣ ሴቶች በበዓሉ የሚያሳዩት አንድነት በቀጣይነትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል።
ሴቶች በሀገር ባህል አሸብርቀው ብቻ ሳይሆን ያላቸውን ተሰጥኦ የሚያሳዩበት መሆኑን ያነሱት ወይዘሮ ትብርህ፣ የሻደይ በዓል ከነፃነት ተምሳሌትነቱ ባለፈ ሴቶች ለልጆቻቸው ልምድ የሚያካፍሉበት ሥርዓት በመሆኑ ይጠናከራል ብለዋል።
ወጣት ብርቱካን ነጋሽ በበኩሏ፣ ሻደይ ሲመጣ በተለያየ ምክንያት የተራራቁ ሴቶችን በማገናኘት በአንድነት የሚያሰባስብ ነው ፣ በበዓሉ ወቅት የሚታየውን ፍቅርና አንድነት በቀጣይም ማጠናከር እንደሚገባ ገልፃለች።
ወይዘሮ ሥንዳይ አስረሴ በበኩላቸው ሻደይን ከልጅነታቸው ጀምረው ሲጫወቱ ያሳለፉ መሆኑን አውስተው፣ በዓሉ አንድነትና ማኅበራዊ እሴትን የሚያጎለብት ነው ብለዋል።
ሻደይን በነፃነትና በፍቅር አክብረው እንዳሳለፉ ሁሉ፣ ልጆቻቸውም የሻደይን እሴት አጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡም ተናግረዋል።