ቀጥታ፡

በክልሉ ለ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ውጤታማነት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው

ሆሳዕና፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፡-በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ለ2019 የትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ውጤታማነት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትልና የመማር ማስተማርና ምዘና ዘርፍ ሀላፊ አቶ ማቲዎስ ማልደዮ እንደገለጹት በክልሉ ለ2019 ትምህርት ዘመን የመማር ማስተማር ሥራ ውጤታማነት የሚረዳ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው።


 

በዚህም በትምህርት ቤቶች የመማሪያ ክፍሎችን የመጠገን፣ ቤተ መጻህፍትንና ቤተ ሙከራዎችን የማደራጀት እንዲሁም  ለመማር ማስተማር ሥራው ምቹ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በትምህርት ዘመኑ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል ከአንድ ሚሊዮን 732 ሺህ በላይ ተማሪዎችን በመመዝገብ ለማስተማር ዝግጅት ተደርጎ የተማሪዎች ምዝገባ መጀመሩን ጠቁመዋል።

በተለይም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሁሉም ሕጻናትን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡


 

እንደ ሃላፊው ገለጻ በክልሉ ከነሐሴ 11 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የተማሪዎች ምዝገባ እየተከናወነ ይገኛል።

በሆሳዕና ከተማ የአለሙ ወልደሃና መካከለኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት ማርታ ሆራሞ በበኩላቸው በትምህርት ቤቱ በ2019 የትምህርት ዘመን ከ1ሺህ 200 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር እየተዘጋጁ ነው።


 

ለእዚህም በአሁኑ ወቅት የመማሪያ ክፍሎችን የማደስ፣ ለመማር ማስተማር ሥራው የሚረዱ ግብአቶችን የማሟላት እና ምቹ የትምህርት ቤት አካባቢ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ልዩ ፍላጎት ላላቸው ተማሪዎችም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ትኩረት መደረጉን ገልጸው፣ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ ለማምጣት ከተማሪ ወላጅ ሕብረት ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። 


 

በከተማው የካቲት 25/67 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህርት መሰረት ታምራት በበኩላቸው፣ በቀጣይ የትምህርት ዘመን ከ3 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን እንደሚቀበሉና ለእዚህም ተማሪዎችን እየመዘገቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በክረምት ወራትም እድሳት የሚፈልጉ መማሪያ ክፍሎችን ከማደስ ባለፈ የተማሪ መቀመጫዎችን የመጠገን እና የትምህርት ቤቱን ቅጥር ግቢ በአረንጓዴ የማስዋብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም