ቀጥታ፡

የኢትዮ-ቻይና ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለቻይና-አፍሪካ ትብብር ትልቅ ተምሳሌት ነው - አምባሳደር ቼን ሃይ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያና ቻይና በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት፣ በቻይና እና አፍሪካ መካከል የጋራ ተጠቃሚነትን ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይ ገለጹ።

ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ ግንኙነቱ ቻይና እና ኢትዮጵያ በሁሉም አጋጣሚዎች አብረው የሚቆሙበትና በጋራ የሚሰሩበት ማዕቀፍ መሆኑን አምባሳደሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ ማለቱ፣ የዓለም አቀፍ ትብብርንና የጋራ ዕድገት አቅም የሚያንጸባርቅ ከመሆኑም በላይ ለቻይና እና አፍሪካ ግንኙነት መጠናከር እንደ ዋና መሠረት እንደሚያገለግልም ተናግረዋል።

ግንኙነቱ ከተለመደው የዲፕሎማሲ ወሰን በመሻገር፣ በጽኑ ፖለቲካዊ እምነትና በጠንካራ ወዳጅነት ላይ ወደተመሰረተ ሁለገብ አጋርነት ማደጉን አመልክተዋል።

በሁለቱ ሀገራት መሪዎች ጥበበኛ አመራር የሁለትዮሽ አጋርነቱ በበርካታ ዘርፎች ጉልህ ውጤት እየተመዘገበበት መምጣቱንም ነው የገለጹት።

በቅርብ ዓመታት በሁለቱ ሀገራት መሪዎች መመሪያ አማካኝነት ቻይና እና ኢትዮጵያ በፖለቲካውና በኢኮኖሚ ዘርፍ በጋራ እየሰሩ ነው ብለዋል።

የሁለቱን ሀገራት ሕዝቦች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ይበልጥ ትብብራቸውን እያጠናከሩ መሆኑን አንስተዋል።

ሁለቱ ሀገራት የደቡብ ንፍቀ ዓለም (Global South) ድምፅ መሆናቸውን ገልጸው በብሪክስ (BRICS) ማዕቀፍ ውስጥ የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

በነዚህ መድረኮች አማካኝነት ቻይና እና ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የጠበቀ ትብብር እንዳላቸው ጠቅሰው፤ ፍትሃዊ የዓለም ስርዓት እንዲሰፍንም በጋራ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህ አጋርነት በረጅም ዘመን ታሪካዊ ወዳጅነት ላይ የተገነባ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደሩ፤ አሁን ላይ የዘመኑን ጥያቄዎች በሚመልስ ፈጣን የእድገት ምዕራፍ ውስጥ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

በአዲሱ ዘመን ሁለንተናዊ ስትራቴጂካዊ አጋርነቱ በከፍተኛ ፍጥነት እንደሚያድግና በጋራ እጣ ፈንታ ላይ የተመሰረተ የቻይና እና አፍሪካ ወዳጅነትን የመገንባት ውጥን ስኬታማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1970 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የሀገራቱ የሁለትዮሽ ትብብር በሁኔታዎች የማይለዋወጥ ስትራቴጂካዊ አጋርነት የተሸጋገረው እ.አ.አ በ2023 ነበር።

የሀገራቱ ግንኙነት ወደዚህ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ደረጃ ማደጉ ይፋ የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቤጂንግ ከተካሄደው ሶስተኛው የቤልት ኤንድ ሮድ (Belt and Road) ጉባኤ ጎን ለጎን ወቅት ከቻይናው ፕሬዚዳንት ሺ ጂንፒንግ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም