ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ መድሀኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟን እያሳደገች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መድሀኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟን እያሳደገች መሆኑን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የመድሀኒት ቅመማ፣ የአካባቢ ጥበቃና ለምግብ ዋስትና ገንቢ ሚና እየተወጣ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጤና አጠባበቅ ፌዴሬሽን ኮንፍረንስ እና ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን "በምሥራቅ አፍሪካ የማይበገር የጤና ኢኮኖሚ መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም እየተካሄደ ነው።

ኮንፍረንሱ ቀጣናዊ የጤና አጠባበቅ ትብብር፣ የሀገር ውስጥ ህክምና ምርት እና የግል አምራቾች የጤናው ተሳትፎን በተመለከተ ትኩረት አድርጎ ይመክራል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ መድሀኒትና የሕክምና መገልገያዎችን በሀገር ውስጥ የማምረት አቅሟን እያሳደገች ነው።

በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ጠንካራ የጤና ተቋማትን መገንባት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በአፍሪካ እንደ ኢቦላ ዓይነት ወረርሽኝ፣ የጤና ደህንነት፣ የፋይናንስና የቴክኖሎጂ ውስንነት የጋራ ስጋት መሆናቸውን ገልጸዋል።

ለዚህ ደግሞ አፍሪካውያን በጋራ መስራት ይገባናል ያሉት ሚኒስትሯ፤ ኢትዮጵያ በጤና አጠባበቅ መሰረታዊ ለውጥ አስመዝግባለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቁን ማህበረሰብ አቀፍ የጤና ተቋም መገንባቷን ገልጸው፤ በጤና ቴክኖሎጂ፣ በሰው ሀብት ልማት በመሰረታዊ የጤና መለኪያዎች መሻሻል ማሳየቱን ገልጸዋል።

ውጤቱ በመንግስትና የግሉ የጤና ተቋማት ዘርፍ የመጣ መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ብለዋል።

የዲጂታል ጤና ስርዓት ምርጫ ሳይሆን አፍሪካውያን ብሔራዊ የጤና አጀንዳቸው ሊያደርጉት እንደሚገባም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የዓለም የጤና ድርጅት ደረጃ ሦስት ማግኘቷን በማንሳት፣ የሀገር ውስጥ የመድሀኒት እና የህክምና መገልገያዎችን ማምረት ቁልፍ አጀንዳዋ ነው ብለዋል።

የአፍሪካን የጤና ስርዓት ለማሻሻል ትብብር ወሳኝ መሆኑን በመግለፅ፣ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር የምታደርገውን ትብብር አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ዶክተር መቅደስ ዳባ አክለው በጤና ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ከአካባቢ ጥበቃ፣ ከምግብ ዋስትና እና ከሥነ-ምግብ ሥርዓት ጋር በጥብቅ የተሳሰሩ በመሆናቸው ለዘላቂ እድገት የተቀናጀ ሥራ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ኢትዮጵያ ከጤና ጎን ለጎን በአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ላይ በስፋት እየሠራች ባለችበት በአሁኑ ወቅት፣ በሥነ-ምግብ እና በምግብ ሥርዓት ዙሪያ የሚከናወኑ ሥራዎችም ተመሳሳይ ጥብቅ ቁርኝት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ እና የኢትዮጵያ ጤና አጠባበቅ ፌዴሬሽኖች ፕሬዝዳንት ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ በበኩላቸው፤ የአፍሪካ ህክምና በአፍሪካ ባለሙያዎች፣ በአፍሪካ ተቋማት መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል።


 

ለዚህ ደግሞ የአፍሪካ የጤና ተቋማትን ከጥገኝነት በማላቀቅ በራሳቸው የጤና ፋይናንስ ማንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለአፍሪካ የጤና አጠባበቅ ሥርዓት የግሉ ዘርፍ የማይናቅ ሚና እንዳለው ገልጸው፤ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ የተመቸ ሥነ ምህዳር መፍጠር እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም