የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያረጋገጥ መድረክ - ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያረጋገጥ መድረክ - ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ሀሳቦች የተንፀባረቁበት መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ እየተቃረበ ነው።
ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፣የምክክር ሂደቱ በሀገሪቱ የነበሩ የቆዩ አለመግባባቶችን ለመፍታት ትልቅ ተስፋ የሰጠ ነው።
የምክክር ጉባኤው በሀሳብ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የመግባባት ባህልን ለመገንባት ጠንካራ መሠረት እየጣለ እንደሚገኝ ጨምረው አስታውቀዋል ።
ተመካካሪ ሚካኤል ታደሰ (ዶ/ር) ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ የምክክር መድረክ መዘጋጀቱ ትልቅና ጠቃሚ ርምጃ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን አሸናፊነት የሚያረጋግጡ የተለያዩ ሃሳቦች እየተንጸባረቁበት ያለ ውጤታማ መድረክ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሌላኛው ተመካካሪ መስፍን ሀበሻ በበኩላቸው ጉባኤው ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን በነፃነት ያንሸራሸሩበት በመግባባት እየተካሄደ የሚገኝ ምክክር መሆኑን ጠቁመዋል።
መድረኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍቅር፣ በሰላም፣ በመተባበርና በመደጋገፍ አብሮ መኖር የሚችል መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ እንደሆነም አስረድተዋል።
በተጨማሪም መንግሥት ዜጎችን የጉዳዩ ባለቤት በማድረግ፣ በማወያየትና በማማከር ወደ መፍትሔ ለመድረስ የወሰደው አቅጣጫ ትክክለኛ ምርጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ሀገራዊ ምክክሩ ተመካካሪዎች ሃሳባቸውን በነፃነት ያነሱበት መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላኛው ተመካካሪ ሀይለማርያም ህሉፍ ናቸው።
ተመካካሪው የግጭትን አጥፊነት፣ የአካልና የሀብት ውድመትን በአካል እንዳዩ ጠቁመው፣ ጦርነት ፍጹም መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል ገልፀዋል።
በማህበረሰቡ ውስጥ ለሚፈጠሩ አለመግባባቶች ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚቻለው በመወያየትና በመመካከር ብቻ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።