የምክክር ጉባኤው የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና የሕዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው- ተመካካሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የምክክር ጉባኤው የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና የሕዝቦችን አብሮነት ለማጠናከር አስተዋጽኦው ከፍተኛ ነው- ተመካካሪዎች
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15 /2018 (ኢዜአ)፦እየተካሄደ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና የሕዝቦችን አብሮነት ይበልጥ ለማጠናከር አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ተመካካሪዎች ገለጹ።
ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወደ ማጠቃለያ ምዕራፍ እየደረሰ ይገኛል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ተመካካሪዎች መካከል ተመካካሪ መምህር ማስረሻ ማሞ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባትና የሕዝቦችን አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።
ለቀጣዩ ትውልድ ዘላቂ ተጠቃሚነት መረጋገጥ የሚበጀው እስካሁን በሀገሪቱ ያልተሞከረውን የምክክር ባህል በማድረግ አጠናክሮ መቀጠል መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ለቆዩ ሀገራዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት እንደ ማኅበረሰብ የሚያስፈልገን መመካከር ነው ያሉት መምህር ማሰረሻ፣ ይህ የምክክር መድረክ ለሀገራችን አዲስ ምዕራፍ እንደሆነም ጠቁመዋል።
ሁልጊዜም ቢሆን መመካከር ዘላቂና አዎንታዊ ውጤት እንደሚያመጣ እንደሚያምኑም ነው የተናገሩት።
ሌላኛው ተመካካሪ በላይ ስዩም በበኩላቸው በምክክር ጉባኤው ባለፉት ጊዜያት ለልዩነት ምንጭ በሆኑ አጀንዳዎች ዙሪያ በጥልቀት መመካከራቸውንና በዚህም ደስተኛ መሆናቸው ተናግረዋል።
ይህ ምክክር ለቀጣዩ ትውልድ መልካም ነገርን ይዞ እንደሚመጣ ሙሉ እምነት እንዳላቸውም አቶ በላይ ገልጸዋል።
ምክክሩ እጅግ አካታች በሆነ መልኩ እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ ሁሉም ተመካካሪዎች በነፃነትና በእኩልነት ሀሳባቸውን እንዲያቀርቡ ዕድል እንደፈጠረም አብራርተዋል።
የሀሳብ ልዩነት በሚፈጥሩ አጀንዳዎች ላይ በመመካከር መፍትሄ ማበጀትን ባህል ማድረግ ቀጣይነት ላለው ሀገረ መንግስት ግንባታ እና ልማትን አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ሌላዋ ተመካካሪ ወይዘሮ አስቴር ጨርቆስ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ለጋራ ችግሮች መደማመጥ ላይ የተመሰረተ ምክክር በማድረግ ምክረ ሀሳቦችን ለማመንጨት የተሄደበት መንገድ እጅግ ደስ የሚልና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።
በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ሁሉም የህብረተሰብ ተወካይ ተመካካሪዎች ያላቸውን ሀሳብ በነጻነት እንዲያነሱ ዕድል መመቻቸቱ የሁሉም ሀሳብ በእኩል እንዲደመጥ አስችሏል ነው ያሉት።
የምክክር ጉባኤው ለኢትዮጵያ ቀጣይ ልማት እና ዘላቂ ሰላም መጎልበት ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑ የገለጹት ደግሞ ሌላኛዋ ተመካካሪ ወንጌላዊት ቤኛ ናቸው።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክሩ ሀገር ጸንታ እንድትቆም የሚያስችል መሠረት የጣለ ታሪካዊ ዕድል እንደሆነም ነው የተናገሩት።