ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤሮስፔስ ዘርፍን ለማሳደግ እና ባለሙያዎችን ለማፍራት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየጣለ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የኤሮስፔስ ዘርፍን ለማሳደግ እና የወደፊት ሙያተኞች ማፍራት የሚያስችል ጠንካራ መሠረት እየጣለ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ላዕከ ታደሰ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀውን የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ "STEM" ትምህርት ሥልጠና መርሐ ግብር ያጠናቀቁ የምረቃ ሥነ ሥርዓት እየተካሄደ ነው።


 

የኢትዮጵያ አቪዬሽን ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ላዕከ እንደገለጹት፤ ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች የተወጣጡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በ"STEM" የትምህርት መርሃ ግብር አማካኝነት የስድስት ሳምንታት ሥልጠና ሲከታተሉ ቆይተዋል።

ተማሪዎቹ በቆይታቸው ከቴክኒክ እውቀት ባሻገር የቡድን ሥራ፣ ሂሳዊ አስተሳሰብ፣ ችግር ፈቺነት እና የፈጠራ ክህሎትን ማዳበር የሚያስችላቸው ሥልጠና መከታተላቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያን የኤሮስፔስ ዘርፍ ለማሳደግ እና የነገ የሀገሪቷን ባለሙያዎች ለማፍራት የሚያስችል ጠንካራ መሰረት እየተጣለ መሆኑንም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ላዕከ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ሲሆን፤ ከቦይንግ ኩባንያ ጋር ለረጅም ዓመታት የቆየ የንግድ እና የቴክኒክ ትብብር እንዳለው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም