ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የህክምና ተቋማትን በመገንባት ለአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15 /2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የህክምና ተቋማትን በመገንባት ለአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነት የመሪነት ሚናዋን እየተወጣች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

13ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የጤና አጠባበቅ ፌዴሬሽን ኮንፍረንስ እና ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን "በምሥራቅ አፍሪካ የማይበገር የጤና ኢኮኖሚ መገንባት" በሚል መሪ ሀሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።


 

ኮንፍረንሱ ቀጣናዊ የጤና አጠባበቅ ትብብር፣ የሀገር ውስጥ ህክምና ምርት እና የግል አምራቾች የጤና ተሳትፎን በተመለከተ ትኩረት አድርጎ ይመክራል።

በመርሃ ግብሩ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ጤና አጠባበቅ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር ማርቆስ ፈለቀ እና ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የህክምና ባለሙያዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የግል ህክምና ዘርፍ አምራቾች ተገኝተዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ አይበገሬ የጤና ስርዓት ያለፈውን የጤና ችግር መቋቋም ብቻ ሳይሆን የቀጣዩን መከላከል  ነው።

የተሟላ ሉዓላዊነት የዜጎችን የጤና ሥርዓት ማሻሻል፣ የመድሀኒትና የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች በራስ አቅም ማምረት መቻል መሆኑንም ገልጸዋል።

የአፍሪካ የጤና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ከመድሀኒትና የህክምና መገልገያ ግብዓት ጥገኝነት መላቀቅ  እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።


 

የፖለቲካ ሉዓላዊነት ያለ ተሟላ የማምረት አቅም ብቻውን የተሟላ አይሆንም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ የአፍሪካ ጠንካራ የጤና ተቋማትና መሰረተ ልማት መገንባት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የአፍሪካን ብልፅግና ለማረጋገጥ ጠንካራ የጤና ሥርዓት በትብብር መገንባት እንደሚገባ ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ለአፍሪካውያን ትብብርና አንድነት ያላት ቁርጠኝነት አዲስ አይደለም ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካ በጠንካራ መሰረተ ልማት የተገነባ የጤና አገልግሎት መስጠት የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገች መሆኑንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የጤና ተቋም በመገንባት የአህጉሪቷ የህክምና ማዕከል ለመሆን እየሰራች እንደምትገኝም አስታውቀዋል።  

አፍሪካ የብቁ ዶክተሮች፣ ሳይንቲስቶች፣ ተመራማሪዎች፣ ሀኪሞች ምድር መሆኗን በማንሳት፤ የሚያስፈልገው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ተቋም መገንባት መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ በማስተባበር በተቋማት ግንባታ ላይ ገንቢ ሚና እየተወጣች ትገኛለች ብለዋል።

ዜጎች ጥራት ያለው፣ ተመጣጣኝና ተደራሽ የጤና አገልግሎት ማግኘት የሚችሉበትን ሥርዓት እየገነባች መሆኗንም ጨምረው ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም