ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰው እና በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የማይመክኑ ኦርጋኒክ በካዮችን ለመቆጣጠርና ለማስወገድ በትኩረት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15 /2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሰው እና በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የማይመክኑ ኦርጋኒክ በካዮችን (POPs) ለመቆጣጠርና ለማስወገድ በትኩረት እየሰራች መሆኑን የኢፌዴሪ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።

ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተሻሻለ የብሔራዊ የትግበራ እቅድ ሰነድ ግምገማ እና ማጽደቂያ መድረክ አካሂዷል።


 

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፍሬነሽ መኩሪያ በዚሁ ወቅት፤ የማይመክኑ ኦርጋኒክ በካዮች በባህሪያቸው ቶሎ የማይበሰብሱ፣ በሰው እና በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ ቁሶች ናቸው ብለዋል።

ከእነዚህ ውስጥም ዲዲቲ (DDT)፣ ፒፎስ (PFOS) እና ፒኤፍኤችኤክስኤስ (PFHxS) የተሰኙትን ለአብነት አንስተዋል።

የማይመክኑ ኦርጋኒክ በካዮች (POPs) የሚያስከትሉትን ጉዳት ለመከላከልና ለማስወገድ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ወይም እንዳይመረቱ የሚያደርግ እኤአ በ2001 የስቶክሆልም ስምምነት መደረጉን አውስተዋል።

ኢትዮጵያ ስምምነቱን መሰረት በማድረግ በሰው እና በአካባቢ ላይ ጉዳት የሚያመጡ የማይመክኑ ኦርጋኒክ በካዮችን (POPs) ለመቆጣጠርና ለማስወገድ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን እንዳከናወነች ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም ለተለያዩ አላማዎች በሚል ይመረቱ የነበሩ እንደ ዲዲቲ (DDT) ያሉ የማይመክኑ በካዮች እንዳይመረቱ እንዲሁም ሀገር ውስጥ ማምከኛ የሌላቸው የተለያዩ ኬሚካሎችን ወደ ውጭ በመላክ እንዲመክኑ መደረጉን አስታውቀዋል።

ዛሬ ለምክክር የቀረበው ሰነድ በሀገር ደረጃ የማይመክኑ ኦርጋኒክ በካዮች አያያዝ፣ ቁጥጥር እና አስተዳደርን የሚያጠናክር ተግባራዊ የስራ መመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

መድረኩ አሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተካሄደ ካለው ሶስተኛ ዙር "ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ" ስራ ጋር ተያያዥነት ያለው እንደሆነም አመላክተዋል።


 

ለብሔራዊ ትግበራ መርሃ ግብሩ ስኬት የፌደራልና የክልል ተቋማት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ የግሉ ዘርፍ፣ የሲቪል ማህበራት እና የልማት አጋሮች ቅንጅት ወሳኝ መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ ጨምረው ተናግረዋል።

አዳዲስ በካይ ኬሚካሎችን መለየት፣ የላቦራቶሪ ቁጥጥር አቅምን ማሳደግ፣ ማምከኛ መሳሪያዎችን መታጠቅ፣ የመረጃ ስብሰባን ማጠናከርና የቴክኒክ እንዲሁም የፋይናንስ አቅምን ማጎልበት የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው ብለዋል።

ከመድረኩ የተገኙት ግብዓቶችን በማካተት ሰነዱን የበለጠ ለማጠናከርና ውጤት ተኮር ለማድረግ እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም