ቀጥታ፡

ረብጣ ገንዘብ ከወጣባቸው ዝውውሮች እስከ አነጋጋሪ የህግ ለውጦች ፡ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዲሱ የውድድር ዓመት ምን ይዞ መጣ?

በሙሴ መለሰ
 
የዓለም እግር ኳስ አፍቃሪያን በጉጉት የሚጠብቀው የ2026/27 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር ዛሬ በይፋ ይጀምራል።

የዘንድሮው የውድድር ዘመን በሰኔ እና ሐምሌ ወራት የተካሄደውን የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ተከትሎ፣ ለተጫዋቾች በቂ የእረፍት ጊዜ ለመስጠት ሲባል ከተለመደው አንድ ሳምንት ዘግይቶ እንዲጀምር ተደርጓል።

የመክፈቻው ጨዋታ በኢምሬትስ ስታዲየም የባለፈው የውድድር ዘመን ሻምፒዮን አርሰናል እና ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ሊጉ በተመለሰው ኮቨንትሪ ሲቲ መካከል ምሽት አራት ሰዓት ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም ይካሄዳል።




ይህ አዲስ የውድድር ዘመን ከመጀመሩ በፊት በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ላይ የፕሪሚየር ሊጉ ክለቦች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል።

እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት፣ የሊጉ ክለቦች ለተጫዋቾች ዝውውር ብቻ ከ2.14 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ ወጪ አድርገዋል።

ይህ የወጪ መጠን የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሌሎች የአውሮፓ አራት ታላላቅ ሊጎች (ስፔን፣ ጣልያን ጀርመንና ፈረንሳይ) በጥምረት ካወጡት የገንዘብ መጠን በላይ ሆኗል።

ሞርጋን ሮጀርስ ከአስቶን ቪላ ወደ ቼልሲ በ117 ሚሊዮን ፓውንድ በመዘዋወር የክረምቱ ውዱ ተጫዋች መሆን ችሏል።

ኤሊዮት አንደርሰን ከኖቲንግሃም ፎረስት ወደ ማንቸስተር ሲቲ በ116 ሚሊዮን ፓውንድ አምርቷል። በተጨማሪም ሳንድሮ ቶናሊ ከኒውካስል ወደ ቶተንሃም በ100 ሚሊዮን ፓውንድ፣ እንዲሁም ብሩኖ ጉማሬሽ ከኒውካስል ዩናይትድ ወደ አርሰናል በ75 ሚሊዮን ፓውንድ መዘዋወራቸው የክረምቱን የዝውውር ገበያ ከሚጠቀሱ ዝውውሮች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

ከዝውውር ወጪው ባሻገር፣ የዘንድሮው የውድድር ዘመን በአዳዲስ አሰልጣኞች የታጀበ ሆኗል። በሊጉ ታሪክ ከፍተኛው በተባለ ደረጃ ዘጠኝ ክለቦች ውድድሩን በአዲስ አሰልጣኞች ይጀምራሉ።



ፔፕ ጋርዲዮላ ማንቸስተር ሲቲን በገዛ ፈቃዱ መልቀቁን ተከትሎ የአርሰናሉ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ አሁን ላይ በሊጉ ረጅም ጊዜ (ሰባት ዓመታት) የቆየው አሰልጣኝ ሆኗል። የቼልሲው ዣቢ አሎንሶ፣ የማንቸስተር ሲቲው ኤንዞ ማሬስካ እና የሊቨርፑሉ አንዶኒ ኢራኦላ ከአዳዲሶቹ አሰልጣኞች መካከል ይጠቀሳሉ።

ማይክል ካሪክ በማንቸስተር ዩናይትድ እንዲሁም ሮቤርቶ ዴ ዜርቢ በቶተንሃም ሆትስፐርስ የመጀመሪያ ሙሉ የውድድር ዓመታቸውን ይጀምራሉ።

የሊጉ የተሳታፊዎች ስብጥርን በተመለከተ፣ ኮቨንትሪ ሲቲ ከ25 ዓመታት በኋላ ከሃል ሲቲ እና ኢፕስዊች ታውን ጋር በመሆን ከታችኛው ሊግ አድገው ሊጉን ተቀላቅለዋል።

በተቃራኒው ዌስትሃም ዩናይትድ፣ በርንሌይ እና ዎልቨርሃምፕተን ዋንደረርስ ባለፈው የውድድር ዘመን መውረዳቸው የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም የእንግሊዝ ክለቦች ባለፈው ዓመት በአውሮፓ ባሳዩት አስደናቂ ብቃት ምክንያት፣ በዚህ የውድድር ዘመን ክብረ ወሰን የሆነ ዘጠኝ የፕሪሚየር ሊግ ክለቦች በአውሮፓ ውድድሮች ላይ ይሳተፋሉ።

አርሰናል፣ አስቶንቪላ፣ ሊቨርፑል፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ በሻምፒዮንስ ሊግ የሚወዳደሩ ሲሆን፣ በርንማውዝ፣ ሰንደርላንድ እና ክሪስታል ፓላስ በዩሮፓ ሊግ እንዲሁም ብራይተን በኮንፈረንስ ሊግ አገራቸውን ይወክላሉ።

የሊጉ አስተዳደር የክለቦችን የፋይናንስ ወጪ የሚቆጣጠር አዲስ የወጪ ገደብ (Squad Cost Ratio) መመሪያን ተግባራዊ አድርጓል።

በዚህም መሠረት ክለቦች ለተጫዋቾች ደሞዝ እና ለዝውውር የሚያወጡት ጠቅላላ ወጪ ከገቢያቸው 85 በመቶ እንዳይበልጥ ተወስኗል። ህጉን የሚጥሱ ክለቦችም የነጥብ ቅነሳ ቅጣት ይገጥማቸዋል።

የጨዋታ ፍጥነትን ለመጨመርና ሰዓት ማባከንን ለመግታት በርካታ አዳዲስ የዳኝነት ህጎች በይፋ ስራ ላይ ይውላሉ።

በእጅ ውርወራ (Throw-in) እና በመልስ ምት (Goal-kick) ላይ ሰዓት ለሚያባክኑ ተጫዋቾች ዳኛው አምስት ሴኮንድ የሚቆጥር ሲሆን፣ ጊዜ ካለፈ እጅ ውርወራው ለተቃራኒ ቡድን ይሰጣል፤ የመልስ ምት ላይ ከሆነ ደግሞ የተቃራኒ ቡድን የማዕዘን ምት ያገኛል።

ሌላው ሰዓት ማባከንን ለመቆጣጠር የወጣው ህግ ተጫዋቾች ታክመው ከወጡ በኋላ ወደ ሜዳ ለመመለስ ቢያንስ አንድ ደቂቃ ውጭ እንዲጠብቁ የሚያስገድደው ደንብ ነው።

በተጨማሪም ተጫዋቾች በሚቀየሩበት ወቅት ከሜዳ ለመውጣት የ10 ሴከንድ ገደብ የተጣለባቸው ሲሆን፣ ይሁንና ጊዜው ካለፈ ተቀያሪው መግባት የሚችለው ጨዋታው በሚቀጥለው ጊዜ ሲቆም ብቻ ይሆናል።




በዚህ የውድድር ዘመን የቪዲዮ ረዳት ዳኛ (VAR) ውሳኔዎችን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ትልቅ ማሻሻያ ተደርጓል።

አንድ ተጫዋች በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲሰናበት አጠራጣሪ ከሆነ ቫር ጣልቃ የመግባት ስልጣን ተሰጥቶታል፤ እንዲሁም በጨዋታ ወቅት በቫር እና በሜዳ ላይ ዳኛው መካከል የሚደረጉ የድምፅ ውይይቶች በሊጉ የጨዋታ ማዕከል በኩል ለደጋፊዎች በቀጥታ ይፋ ይደረጋሉ።

በአጠቃላይ፣ የዘንድሮው የ2026/27 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዘመን ከአዳዲስ የህግ ለውጦች፣ ከከፍተኛ የዝውውር ወጪዎች እና አዳዲስ የአሰልጣኞች ሹመት ጋር ተያይዞ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረትን ስቧል።

አርሰናል የዋንጫ ክብሩን ለማስጠበቅ፣ ማንቸስተር ሲቲ ያለ ፔፕ ጋርዲዮላ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር፣ እንዲሁም አዳዲስ አሰልጣኞችና ክለቦች ህልማቸውን ለማሳካት የሚያደርጉት ፍልሚያ የእግር ኳስ አፍቃሪያን እስከ ግንቦት ወር መጨረሻ ድረስ የሚዘልቅ አስደሳች እና አጓጊ የእግር ኳስ ጊዜን እንደሚያሳልፉ አያጠራጥርም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም