ቀጥታ፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ባህል እየጎለበት መምጣቱ ለደም ማሰባሰብ ስራው ውጤታማነት አቅም ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባር ባህል እየጎለበተ መምጣቱ ለደም ማሰባሰብ ስራው ውጤታማነት አቅም እየፈጠረ መሆኑን የኢትዮጵያ ደምና ሕብረህዋስ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ገለጹ።

የአገልግሎቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ታዬ ቀደም ሲል በህክምና ተቋማት ለሚያቀርቡት የደም አቅርቦት ጥያቄ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት አስቸጋሪ ከሆኑ ወቅቶች መካከል የክረምት ወቅት ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

ደም በተቀናጀ መንገድ የሚሰበሰብባቸው ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት እና የክረምቱ ነባራዊ ሁኔታም በደም አሰባሰቡ ላይ የራሱ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለው አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ከሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት መካከል አንዱ የደም ልገሳ መርሃ ግብር መሆኑ በክረምት ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የደም አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በመሆኑም አገልግሎቱ የዘንድሮ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን ምክንያት በማድረግ ከተለያዩ በጎ ፈቃደኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ከበጎ ፈቃደኞች ደም የማሰባሰብ ስራውን በተጠናከረ መንገድ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ከሐምሌ 1 ቀን 2018 እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ በሀገር አቀፍ ደረጃ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት 150 ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ መታቀዱንና እስካሁን 95 ሺህ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልጸዋል።

የደም ማሰባሰብ ስራው በሀገሪቱ በሚገኙ የደም ባንክ ተቋማት፣ ደም በሚሰበሰብባቸው ማዕከላት እየተከናወነ መሆኑንና ይህም የደም አቅርቦቱን በማሳለጥ የደም ፍላጎትን የማሟላት አቅምን እያጎለበተ መምጣቱን ተናግረዋል።

የደም አቅርቦት በመሻሻል የደም ፍላጎትን በሚገባ ተደራሽ ለማድረግ አገልግሎቱ በክልሎች ደም የሚሰበስብባቸውን ማዕከላት የማስፋፋት ስራውን አጠናክሮ መቀጠሉንም ተናግረዋል።

አገልግሎቱ አሁን ላይ በሀገሪቱ ደም የማሰባሰብ ስራ የሚሰራባቸውን የደም ባንኮች ቁጥር 63 ማድረሱንም አቶ ሀብታሙ ጠቁመዋል።

የሚሰበሰበው ደም ተገቢውን የምርመራ ሂደት እንዲያልፍ በማድረግ ለታካሚው ለማድረስ አገልግሎቱ የላቦራቶሪ ማሽኖችን ወደ ስራ የማስገባት፣ አሰራሮችን የማዘመን ስራ በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።

ከበጎ ፈቃደኞች ደም የማሰባሰብ ስራ ከኦ ኔጌቲቭ የደም አይነት ጋር ተያይዞ ሊኖር የሚችለውን እጥረት በመቅረፍ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው አቅርቦቱን ለማሳደግ የኦ ኔጌቲቭ የሆኑ ማህበራትን ያሳተፈ ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ አገልግሎቱ የደም አቅርቦትን ወጥነት ባለው መንገድ ለማከናወንና የደም ተዋጽኦ ምርቶችን የማምረት አቅም ማሳደግ ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራበት አመላክተዋል።

በመጨረሻም ኅብረተሰቡ በበጎ ፈቃድ በክረምቱ እያደረገ ያለውን ደም የመለገስ ሰብዓዊ ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

ሜክሲኮ አካባቢ ባለው የደም ማሰባሰቢያ ቦታ ላይ ደም ስትለግስ ያገኘናት ሜሮን እስጢፋኖስ ደም መለገስ በጎ ተግባርን በመፈጸም ደስታንና የጤና ጥቅም የምናገኝበት በመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ መለገሷን ገልጻለች።

ደም መለገስ በደም እጥረት ምክንያት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች መድረስ በመሆኑ ደሜን ለግሻለሁ ስትል ተናግራለች።

ሌላኛው ደም ሲለግስ ያገኘነው ዮናስ ሽፈራው ከ12 ጊዜ በላይ ደም መለገሱን ገልጾ በአደጋዎች ምክንያት ህክምና ላይ ለሚገኙ ወገኖቹ ለመድረስ የሚተካውን ደም በመስጠት የማይተካውን የሰው ህይወት ለመታደግ ደም እየለገሰ እንደሚገኝ ገልጿል።

በየጊዜው ደም መለገሱ የህሊና እረፍት የሚሰጥ ሰብአዊ ተግባር በመሆኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጥቀስ ወጣቶች ደም የመለገስ ባህላችንን በማጎልበት የሰው ህይወት እናድን ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ደም መለገስ የአእምሮ ደስታን የሚሰጥ በጎ ተግባር ነው ያሉት ደግሞ አቶ ዮሐንስ አመኔ ናቸው።

ዛሬ የምናደርገው በጎ ተግባር ነገ ላይ ለራሳችንም የሚጠቅም በመሆኑ ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከኢትዮጵያ ደምና ሕብረሕዋስ ባንክ አገልግሎት በሜክሲኮ አደባባይ የደም ማሰባሰብ ስራውን እያስተባበሩ ያሉት እያሱ ኤርጊቾ ሰዎች ደም እንዲለግሱ ከበጎ ፈቃደኞች ጋር እየሰራን እንገኛለን ብለዋል።

በክረምቱ የደም ማሰባሰብ ስራው ውጤታማ እንዲሆን ከበጎ ፈቃደኞች ደም የመሰብሰብ ስራውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማከናወን ደህንነቱን በተጠበቀ መንገድ እየሰሩ እንደሚገኙም አክለዋል።

በጎ ፈቃደኛ መክሊት ፀጋዬ በበኩሏ በልዩ ልዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እየተሳተፈች እንደምትገኝ ጠቁማ ዘንድሮም የደም ልገሳ መርሀ ግብር ውጤታማ እንዲሆን በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን በማስተባበር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ደም እንዲለግሱ እያደረገች መሆኗን ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም