ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የግብርና ምርቷን ለማሳደግ በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ላይ በትኩረት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ የግብርና ልማትን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በመስኖ ልማት፣ በተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችና በግብርና ሜካናይዜሽን ላይ በትኩረት እየሰራች መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ ገለጹ።

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን (ኢጋድ) አባል ሀገራት አምባሳደሮች ኮሚቴና የኢጋድ ፓርላማ ፎረም በአግሪፉድ ሲስተም ዙሪያ በአዲስ አበባ ያዘጋጁት ከፍተኛ የልምድ ልውውጥ መድረክ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሰለሞን ላሌ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የግብርና ልማትን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ በመስኖ ልማት፣ በተሻሻሉ ምርጥ ዘሮችና በግብርና ሜካናይዜሽን ላይ በትኩረት እየሰራች ነው።




የክላስተር እርሻ ልማት አርሶ አደሮች የግብዓት፣ የቴክኖሎጂ፣ የባለሙያ ምክክር አገልግሎትና የገበያ ትስስሮችን በተሻለ ሁኔታ እንዲያገኙ እያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በአረንጓዴ ዐሻራ እና በሌማት ትሩፋት ተነሳሽነቶች የአካባቢ ጥበቃን፣ የግብርና ምርታማነትንና የቤተሰብ ምግብና የአመጋገብ ስርዓትን ለማሻሻል ትኩረት መሰጠቱን ገልጸዋል።

የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ተወካይና በድርጅቱ የውጭ አገልግሎት ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር ኦማር ጃማ የአግሪፉድ ሲስተም ለውጥ የካምፓላ የግብርና ልማት ቃል ኪዳንን ወደ ተግባር በማሸጋገር፣ በጠንካራ ፖሊሲ፣ የሕግ ማዕቀፍ፣ በጀትና ኢንቨስትመንት በመደገፍ እንደሚሳካ ጠቁመዋል።




ሀገራቱ ለምግብ ዋስትና ችግር፣ ለአየር ንብረት ለውጥ፣ ለዝቅተኛ ምርታማነትና ለውስን የገበያ ትስስር የተጋለጡ በመሆኑ፣ የግብርና ለውጥን ለማፋጠን አባል ሀገራት የተቀናጀ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር ይገባቸዋል ብለዋል።

በመድረኩ የአግሪፉድ ሲስተም ልማትን ለማፋጠን የፖሊሲ ቅንጅትን፣ የግብርና ኢንቨስትመንትን፣ የቀጣናዊ ንግድ ትስስርንና የፓርላማ ክትትልን ማጠናከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም