ቀጥታ፡

የትግራይ ህዝብ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የሚያደርስበትን የግፍና መከራ ለማስቆም ትግሉን ማጠናከር አለበት-የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ

አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 15/2018(ኢዜአ)፦የትግራይ ክልል ህዝብ ሕገወጡ የሕወሓት ቡድን በክልሉ እያደረሰበት ያለውን ግፍና መከራ ለማስቆም ትግሉን ማጠናከር እንዳለበት የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ ሊቀ መንበር ከበደ አሰፋ ገለጹ።

ቡድኑ ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የጥፋት ጥምረት በመመስረት ሀገሪቷን ከቀይ ባህር በማራቅ ለደህንነት ስጋት ከዳረገበት እኩይ ተግባሩ ባለመታቀብ ዛሬም የባዕዳንን ተልዕኮ በማስፈጸም ላይ መሆኑንም ገልጸዋል።

የትንሳኤ ሰባ አንደርታ ፓርቲ ሊቀ መንበር ከበደ አሰፋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ህገ ወጡ የሕወሃት ቡድን ከታሪካዊ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር የጥፋት ጥምረት መመስረት ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር በማራቅ ለደህንነት ስጋት ከዳረገበት እኩይ ተግባሩ የቀጠለ ተልዕኮ የማስፈጸም ሂደት ነው።

ሕገ-ወጡ ቡድኑ "ፅምዶ" በሚል ስም ከሻዕቢያ የጥፋት ሀይል ጋር የፈጠረው የጥፋት ጥምረት ኢትዮጵያን ለማፍረስና ከዘላቂ ልማቷ ለማደናቀፍ የተወጠነ የባዕዳን ተልዕኮ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ሕገ-ወጥ ቡድን ከምስረታው ጀምሮ የኢትዮጵያዊነት ሥነ-ልቦና የነበራቸውንና ድብቅ አጀንዳውን የተረዱ የትግራይ ተወላጆችን በማጥፋት እና በማስወገድ የፈጸማቸው እኩይ ተግባራቱ ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን አክለዋል።

ኢትዮጵያን ከቀይ ባህር በማራቅ ለደህንነት ስጋት እንድትጋለጥ ማድረጉ አስታውሰው፤ ሕገ-ወጥ ቡድኑ ከምስረታው ጀምሮ ለሀገርም ሆነ ለትግራይ ክልል ህዝብ ጥቅም መከበር ከመቆም ይልቅ ለባዕዳን ሀይሎች ተልዕኮ መገዛቱን ያሳያል ብለዋል።

ይህ ሕገ-ወጥ የሕወሃት የጥፋት ቡድን ለሰሜኑ ጦርነት መቀስቀስ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚያም በኋላ የፕሪቶሪያውን ስምምነት መጣሱና የጥፋት መንገድ መከተሉ የህገ ወጥ ቡድኑን ለባዕዳን የመላላክ ተፈጥሯዊ ባህሪው መሆኑን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።

ሻዕቢያን ጨምሮ ከሌሎች የጥፋት ቡድኖች ጋር ያልተቀደሰ ጥምረት መመስረቱ ኢትዮጵያ ዘላቂ ልማቷን እንዳታረጋግጥና አሁንም ሀገሪቷን ለማመስ የተዘረጋ የባዕዳን ፕሮጀክት አካል መሆኑንም አመልክተዋል።

ሕገ-ወጥ የሕወሃት ቡድን የጥፋት ተልዕኮን ለመፈጸም "ፅምዶ" በሚል መጠሪያ ከሻዕቢያ መንግስት ጋር የፈጠረው ጥምረት ኢትዮጵያን ከልማቷ እና ከሰላሟ ወደ ኋላ ለማስቀረት የተወጠነ የባዕዳን ሀይሎች እኩይ ሴራ እንደሆነም ገልጸዋል።

የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት በትግራይ ክልል ወጣቶች መስዋዕትነት ለማስፈጸም የሚደረገው ጥረት፣ በህዝቡና በወጣቱ ንቃት ምክንያት እንደፈለገው ሊሳካ አለመቻሉን ተናግረዋል።

ሕገ-ወጡ ህወሓት የላኪዎቹን ተልዕኮ ለመፈጸም ጥረት የሚያደርግ ቢሆንም፤ የትግራይ ክልል ህዝብ፣ ወጣቱና ምሁራኑ ከቡድኑ ትክክለኛ ማንነት ከየትኛውም ጊዜ በላይ አሁን ላይ መረዳታቸውን ጠቁመዋል።

በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ትግራይ ክልል ተወላጆች ይበልጥ በመደራጀትና በመተጋገዝ ለቀውሱ ምክንያት የሆነውን አካል በፍጥነት በማስወገድ ረገድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

በውጭ ሀገር የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆችም አስፈላጊውን ተፅዕኖ በማሳደር ቡድኑ እያደረሰ ያለውን ግፍና መከራ ለማስቆም መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም