ቀጥታ፡

በኦሮሚያ ክልል ተመናምኖ የነበረው የደን ሽፋን በአረንጓዴ አሻራ አማካኝነት በፍጥነት እያደገ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተከናወኑ ተግባራት አማካኝነት ተመናምኖ የነበረው የደን ሽፋን መልሶ እድገት እያሳየ መሆኑን የክልሉ ደን እና ዱር እንስሳት ድርጅት አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና
ብዝሃ-ሕይወት ባለቤት ቢሆንም፣ ባለፉት አሥርተ ዓመታት በሕገ-ወጥ የደን ምንጣሮ፣ ለእንጨትና ከሰል ምርት በሚደረግ ጭፍጨፋ እና ለእርሻ መሬት ማስፋፊያ ምክንያት የደን ሽፋኑ በከፍተኛ ደረጃ ተመናምኖ ቆይቷል።

ይህ የደን ውድመት አካባቢውን ለአፈር መሸርሸር፣ ለወንዞችና ሐይቆች መድረቅ እንዲሁም ለምርታማነት መቀነስ ዳርጎት የነበረ ሲሆን፣ በተለይም እንደ ሐረማያ ባሉ አካባቢዎች የነበሩ የውሃ አካላት ሙሉ በሙሉ እስከመድ
ረቅ ደርሰው የነበረው አካባቢያዊ ሥነ-ምህዳሩ ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጦ ስለነበር ነው።

ይህንን ሥነ-ምህዳራዊና ምጣኔ-ሀብታዊ አደጋ ለመቀልበስ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ በሀገር ደረጃ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉም በየዓመቱ እንደ ዋነኛ መፍትሔ ተወስዶ ሰፊ የተቀናጀ ንቅናቄ በማካሄድ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ውጤት እየመጣ ነው።

የኦሮሚያ ክልል ደን እና ዱር እንስሳት ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ አራርሳ ረጋሳ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ በክልሉ ባለፉት ዓመታት የደን ሽፋኑን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል።

በክልሉ የደን ሽፋኑን ለማሳደግ ከተከናወኑት ተግባራት መካከል፣ በተለይም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተራቁተው በነበሩ ቦታዎች ላይ ሳይንሳዊ መንገድን በተከተለ መልኩ የተለያዩ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን አካባቢዎችን ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እንዲሁም ሕገ-ወጥ የእርሻ መሬት ማስፋፋትን ለመግታት በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።

በተለይም ችግኞችን በመትከል ላይ ብቻ ሳይወሰን ለእንክብካቤያቸው ከፍተኛ ትኩረት በመሰጠቱ ለውጤቱ ዋነኛ ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል።

በዚህም በክልሉ ከዚህ በፊት ተመናምኖ የነበረው የደን ሽፋን ወደ 27 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል።

ይህ የተቀናጀ ጥረት የአፈር መንሸራሸርን መከላከል፣ የአፈር ለምነትን መመለስ እንዲሁም የደረቁ ምንጮች፣ ሀይቆችና ወንዞች እንደገና እንዲጎለብቱ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም በምስራቅ ሀረርጌ ዞን ደርቆ የነበረው የሐረማያ ሀይቅ ሙሉ በሙሉ ማገገሙን ለአብነት አንስተዋል።

በአጠቃላይ የመርሃ ግብሩ ስኬት በሁሉም ወቅቶች መሬትን በማልማት፣ የአካባቢ ጥበቃን ከግብርና ስራዎች ጋር በማጣመር የምርትና ምርታማነት እድገትን ከማሳደግ አንጻር ከፍተኛ ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አቶ አራርሳ እንደገለጹት፣ በአሁኑ ወቅት በክልሉ በአጠቃላይ 4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን መልማቱን ገልጸዋል።

ከአጠቃላይ መሬቱ ውስጥ 1 ሚሊዮን ሄክታር ያህሉ ለዱር እንስሳት እንክብካቤና ጥበቃ፣ ለፓርኮች፣ ለስፖርት ስፍራዎች ሲሆኑ፣ 700 ሺህ ሄክታር መሬት ደግሞ ለችግኝ ተከላ እና ለሰው ሰራሽ ደን ልማት የተመደበ ስፍራ ነው።

ከአጠቃላይ መሬቱ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ደግሞ ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ ደን የተሸፈነ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም