ኢትዮጵያ በማህበረሰብ አቀፍ እና አማራጭ የፍትሕ ስርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አብነት የሚሆን ስራ እያከናወነች ነው -በኔዘርላንድስ ሄግ የሚገኘው የሕግ ፈጠራ ተቋም - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በማህበረሰብ አቀፍ እና አማራጭ የፍትሕ ስርዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ ረገድ አብነት የሚሆን ስራ እያከናወነች ነው -በኔዘርላንድስ ሄግ የሚገኘው የሕግ ፈጠራ ተቋም
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ አማራጭ ሀገር በቀል የክርክር መፍቻ ስልቶችን ወደ ማህበረሰቡ በማቅረብ የፍትሕ ስርዓቷን ለማሻሻል የምታደርገው ጥረት በአብነት የሚጠቀስ መሆኑን ተቀማጭነቱን በኔዘርላንድስ ሄግ ያደረገው የሕግ ፈጠራ ተቋም (HiiL) አስታወቀ።
የተቋሙ ዋና ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ሼካር ፑላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፥ ኢትዮጵያ የማህበረሰብ ፍትሕ ማዕከላትን (CJCs) ተደራሽነት እያሰፋችበት ያለችበትን መንገድ እና የሀገር ሽማግሌዎችን በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ለማካተት የምታደርገውን ጥረት አድንቀዋል።
ይህ አማራጭ የበለጠ ተደራሽ፣ ቀልጣፋ እና ሰላማዊ የፍትሕ ስርዓትን ለመገንባት የሚያስችል ተምሳሌታዊ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በማህበረሰባዊ የፍትሕ አማራጭ እና አዳዲስ የፍትሕ መስጫ መንገዶች በእርግጥም ከግንባር ቀደም ሀገራት አንዷ ናት ብለዋል።
የፍትሕ ሚኒስቴር ከአማራጭ የክርክር መፍቻ ዘዴዎች እና ህዝብን ማዕከል ካደረገ የፍትሕ አሰራር ጋር በተያያዘ ላሳየው ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ አመርቂ ስራ እያከናወነች ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መልካም ተሞክሮዎችን እየቀሰመች ልምዷን ለሌሎች ሀገራት የማካፈል ትልቅ አቅም እንዳላት አንስተዋል።
በተለይም ባለፈው ዓመት በሲዳማ ክልል የማህበረሰብ ፍትሕ ማዕከል በተከፈተበት ወቅት ያደረጉትን ጉብኝት በማስታወስ፣ የፍትሕ ስርዓቱ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ያለውን አዎንታዊ ግንኙነት አድንቀዋል።
በጉብኝታቸው የፍትሕ ሚኒስቴር ለባህላዊ መሪዎች ያለውን አክብሮት ለመመልከት መቻላቸውንና ዘመናትን ያስቆጠሩ የማህበረሰብ አቀፍ የክርክር መፍቻ ልምዶቻቸው ከመደበኛው የፍትሕ ስርዓት ጎን ለጎን እንዴት መስራት እንደሚችሉ መመሪያ መስጠቱን አውስተዋል።
ይህ የፍትሕ አማራጭ ትልቅ ተስፋ ያለው፣ ሊሰፋ የሚችል እና ወደፊት ኢትዮጵያን በጥሩ ሁኔታ ሊጠቅም የሚችል አሰራር ነው ብለዋል።
መደበኛ ያልሆነ የፍትሕ አሰጣጥ ስርዓት አለመግባባቶችን በፍጥነት ለመፍታት እና የበለጠ ሰላማዊ ማህበረሰብ ለመገንባት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል።
ይህ አማራጭ ህዝቡ ወደ ዋና ዋና ከተሞች ወይም ወደ ሩቅ ፍርድ ቤቶች ከመጓዝ ይልቅ ባለበት ማህበረሰብ ውስጥ ፍትህን በቅርበት ማግኘት እንደሚችል ገልጸዋል።
ለባህላዊ መሪዎች የተዘጋጁ መመሪያዎች የማህበረሰብ እሴቶችን በጠበቀ መልኩ፣ አለመግባባቶችን በመፍታት ረገድ የበለጠ ወጥ እና መረጃን መሰረት ያደረጉ አማራጮችን በማሳደግ ስርዓቱን የበለጠ ሊያጠናክሩት እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያ የፍትሕ ማሻሻያ ጥረቶች ማዕከል የሆነው እ.አ.አ. በ2019 የተካሄደው የፍትሕ ፍላጎት እና እርካታ ጥናት መሆኑን ጠቅሰው፤ ጥናቱ በፍትሕ ስርዓቱ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ለመለየት የረዳ እና ህዝብን ማዕከል ያደረጉ ማሻሻያዎች ላይ አስፈላጊ መሰረት የጣለ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አውስተዋል።
ጥናቱ የፍትሕ አገልግሎቶችን በዜጎች እውነተኛ ፍላጎቶች እና ተሞክሮዎች ዙሪያ የመቅረፅን አስፈላጊነት ያሳየ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
በብዙ ሀገራት እንሰራለን፤ በፍትሕ ሚኒስቴር በኩል ያለው ቁርጠኝነት ግን አርአያነት ያለው ነው ብለዋል።
የሕግ ፈጠራ ተቋም (HiiL) ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ግንኙነት እ.ኤ.አ. በ2019 ከቀድሞው ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከተፈረመበት ጊዜ አንስቶ የዘለቀ ነው።
ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተቋሙ በሲዳማ እና አፋር ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች የመደበኛ ፍትሕ ተቋማትን ማህበረሰብ አቀፍ እና ባህላዊ አሰራሮች ጋር የማስተሳሰር ስራን እንዲሁም የማህበረሰብ ፍትሕ ማዕከላትን ሲደግፍ ቆይቷል።
ይህ እንቅስቃሴ ፍትህን ተደራሽ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ በተለይም በቦታ፣ በፋይናንስ ወይም በተቋማት ምክንያት ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች ተደራሽ ያልሆኑ ዜጎች ምላሽ ሰጪ ለማድረግ የሚደረገውን ሰፊ ጥረት የሚያንጸባርቅ ነው።
የፍትሕ አገልግሎቶችን ወደ ማህበረሰቡ በማቅረብ እና ባህላዊ ተቋማት በግልጽ ማዕቀፍ ውስጥ አስተዋጽኦ የሚያደርጉበትን እድል በመፍጠር፣ ኢትዮጵያ የካበቱ የማህበረሰብ ልምዶችን ከዘመናዊ የፍትሕ አማራጮች ጋር ለማዋሃድ እየሰራች ይገኛል።
ይህም ኢትዮጵያ የቆዩ ቅሬታዎችን ለመፍታት፣ ማህበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እና አለመግባባቶችን ለመፍታት የበለጠ ሰላማዊ የአሰራር ዘዴዎችን ለመገንባት እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ ሂደት እና የሀገራዊ የምክክር ስራዎችን እያከናወነች ባለችበት በአሁኑ ወቅት የመጣ ትልቅ አጋጣሚ ነው።
ለሄግ የሕግ ፈጠራ ተቋም (HiiL) የኢትዮጵያ ተሞክሮ ከሀገሪቷ ባሻገር ለሌሎች ሀገራት መልካም ትምህርቶችን የሚሰጥ መሆኑን ኦፊሰሩ ተናግረዋል።