በክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 15/2018(ኢዜአ) ፦ በክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት ዜጎችን ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን በብልጽግና ፓርቲ የሀረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ጌቱ ወዬሳ ገለጹ።
የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የብልፅግና ፓርቲ ሰው ተኮር እሳቤ ተግባራዊ መገለጫ መሆኑንም አቶ ጌቱ ተናግረዋል።
የሀረሪ ክልል ብልፅግና ፓርቲ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎትና ኢኒሼቲቮችን አፈፃፀም በገመገመበት ወቅት አቶ ጌቱ ወዬሳ እንደገለፁት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት አምጥተዋል።
በተለይ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈቱና ተጠቃሚነትን ለሚያረጋግጡ ተግባራት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።
በዚህም የአረጋውያንና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት እድሳትና መልሶ ግንባታ፣ የአካባቢ ንጽህና ጥበቃ፣ ችግኝ ተከላ፣ ደም ልገሳ፣ የማጠናከሪያ ትምህርት መስጠትና የትምህርት ቁሳ ቁስ ድጋፍ የማሰባሰብ ስራዎች መጠናከራቸውን ቀጥለዋል።
የክረምት በጎ ፈቃድ ተግባራት የብልፅግና ፓርቲ ሰው ተኮር እሳቤ ማሳያ ነው ያሉት ኃላፊው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በሌላ በኩል አመራሩ ለፋይዳ ብሄራዊ መታወቂያ እና የ 7 ሚሊየን ኮደርስ ስልጠና ልዩ ትኩረት በመስጠት እንዲሰራ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በክልሉ አምራችና ሸማቹን በቀጥታ በማገናኘት የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የተጀመሩ የቅዳሜ ገበያዎች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ገልፀዋል።