የተወዳጁ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ የውድድር ዘመን በሻምፒዮኑ አርሰናል እና ኮቨንተሪ ሲቲ ጨዋታ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የተወዳጁ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አዲስ የውድድር ዘመን በሻምፒዮኑ አርሰናል እና ኮቨንተሪ ሲቲ ጨዋታ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ የ2026/27 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ጅማሮውን ያደርጋል።
ምሽት አራት ሰዓት ላይ አርሰናል ከኮቨንተሪ ሲቲ ጋር በኤምሬትስ ስታዲየም ጨዋታውን ያደርጋል።
አርሰናል የወቅቱ የፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮን ነው። ተጋጣሚው ኮቨንተሪ ሲቲ ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ተመልሷል።
ሁለቱ ቡድኖች በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሲገናኙ የአሁኑ ለ19ኛ ጊዜ ነው።
ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 18 ጨዋታዎች አርሰናል 10ሩን በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ኮቨንተሪ ሲቲ ሦስት ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪ አምስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
አርሰናል በ18ቱ ጨዋታዎች ላይ 25 ጎሎችን ሲያስቆጥር ኮቨንተሪ ሲቲ 13 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ሁለቱ ቡድኖች ለመጨረሻ ጊዜ በሊጉ የተገናኙት እ.አ.አ በ2001 ነበር።
በወቅቱ ባደረጉት ጨዋታ አርሰናል በዴኒስ ቤርካምፕ ጎል 1 ለ 0 አሸንፏል። ኮቨንተሪ ሲቲ በዛው ዓመት ከሊጉ ወርዷል።
ኮቨንተሪ በፍራንክ ላምፓርድ እየተመራ በሻምፒዮንሺፑ በ95 ነጥብ አንደኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ ከ25 ዓመታት በኋላ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ተመልሷል።
በማይክል አርቴታ የሚመራው አርሰናል የሻምፒዮንነት ክብሩን የማስጠበቅ ጉዞውን ከአዲስ አዳጊው ክለብ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ይጀምራል።
ኮቨንተሪ ሲቲ በመጀመሪያው የሊግ ጨዋታው ከሊጉ የወቅቱ የዋንጫ ባለቤት ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
የ36 ዓመቱ ቶም ብራሞል የመክፈቻውን ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመራሉ።
የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።