ቀጥታ፡

ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለማበጀት ትልቅ ዕድል የፈጠረው-ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦የሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ለጋራ ችግሮች የጋራ መፍትሔ በማበጀት የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ተመካካሪዎች ገለጹ።

ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወደ ማጠቃለያ ምዕራፍ ደርሷል።

ከተመካካሪዎቹ መካከል ረዳት ፕሮፌሰር አብዱልወኪል ሀሰን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት እንደገለጹት፥ ምክክሩ የአሳታፊነት መርሆዎችን በጠበቀ መልኩ እየተካሄደ ነው።

ለምክክር በቀረቡ አጀንዳዎች ላይ ሁሉም ተመካካሪ ሀሳቡን በነጻነት ያንሸራሸረበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ለነገዋ የተሻለች ኢትዮጵያ ግንባታ የሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ጥሩ ልምድ መሆኑን ተናግረዋል።

ምክክሩ ኢትዮጵያን ለመገንባት የሚያስችል ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸው፤ ምክክር ለችግሮች መፍቻ ቁልፍ መሆኑን አመልክተዋል።

ሌላዋ ተመካካሪ ዓለምፀሐይ ተስፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በምክክሩ በተደረጉ የቡድን ውይይቶች የተለያዩ ሀሳቦች በሚገባ የተንሸራሸሩ መሆኑን ገልጸዋል።

"ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው፤ እዚህ የተሰባሰብነውም ዘላቂ ሰላም የመገንባት ሀገራዊ ውጥን ውጤታማ እንዲሆን መሰረት ለማኖር ነው" ብለዋል።

ምክክሩ የኢትዮጵያን ቋጠሮዎች ለመፍታት ሁነኛ መንገድ በመሆኑ በዚህ ታሪካዊ ሂደት ላይ በመሳተፌም እጅግ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

በምክክሩ ላይ ለኢትዮጵያ ይበጃሉ ያልናቸውን ሀሳቦች ሁሉ አቅርበናል ያሉት ደግሞ ሌላው የምክክሩ ተሳታፊ አሳምነው ዋቅጅራ (ዶ/ር) ናቸው።

የምክክር መድረኩ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያን ያማከለና ሁሉንም አካታች ያደረገ ጥሩ ውይይት የተካሄደበት መሆኑን ተናግረዋል።

የምክክር ሂደቱ ውጤታማ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአጠቃላይ ድምር ውጤቱም ሀገርን የሚያሻግሩ ውጤቶችን እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም