ቀጥታ፡

አረንጓዴ አሻራ ከአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ጋር መቀናጀቱ ውጤታማ አድርጎናል-አርሶ አደሮች

ገንዳውሃ፤ ነሐሴ 15/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ጋር በማቀናጀት ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ የቆላ ፍራፍሬ ልማትን በኩታ ገጠም እርሻ ለማልማት ትኩረት ተሰጥቶ እየተከናወነ ይገኛል።

በልማቱ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል አርሶ አደር ደሴ ባይተኩስ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ጋር አስተሳስረው በመስራታቸው አመርቂ ውጤት አግኝተዋል።


በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያለሙትን ሙዝና ማንጎ ለገበያ በማቅረብ ከ150 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ነው የሚናገሩት።

በተለይ "በክላስተር መደራጀታችን የውሃ አጠቃቀማችንን እና የግብዓት አቅርቦት ችግራችንን አቃልሎልናል" ያሉት አርሶ አደሩ፣ በዘንድሮው ዓመትም የተሻለ ምርት ለማግኘት እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የወረዳው ነዋሪ አርሶ አደር ፀጋነሽ ብዙነህ በበኩላቸው፥ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት በስፋት ለመሳተፍና ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስችል ዕድል ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።

ሁለት ሄክታር በሚጠጋ መሬት ካለሙት ሙዝ፣ ማንጎና
 ፓፓያ ከእለት ፍጆታ በተጨማሪ ለገበያ የሚተርፍ ምርት በማምረት ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

የምዕራብ ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አንዳርጌ ጌጡ እንዳሉት፥ በዞኑ በ1 ሺህ 113 ሄክታር መሬት ላይ የቡናና የቆላ ፍራፍሬ ልማት እየተካሄደ ይገኛል።

ከዚህ ውስጥ 200 ሄክታሩን በክላስተር በፓፓያና በሙዝ ለማልማት በተጀመረው ስራ እስካሁን ከ40 ሄክታር በላይ መሬት መሸፈኑን ገልጸዋል።

የፓፓያና የሙዝ ክላስተር ልማትን ይበልጥ ለማስፋፋት መምሪያው ልዩ ትኩረት መስጠቱን የጠቀሱት ኃላፊው፥ አስፈላጊው ግብዓት በወቅቱ ለአርሶ አደሮች እንዲሰራጭ መደረጉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም