ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የዓለም ንግድ ድርጅት የሁለትዮሽ ገበያ ዕድል ስምምነት ተፈራረመች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የዓለም ንግድ ድርጅት የሁለትዮሽ ገበያ ዕድል ስምምነት ተፈራረመች
አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር በዓለም ንግድ ድርጅት (WTO) አባልነት ሂደት ማዕቀፍ ስታካሂድ የቆየችውን የሁለትዮሽ የገበያ ዕድል ድርድር በስኬት በማጠናቀቅ የስምምነት ሰነድ ተፈራርማለች።
የስምምነት ሰነዱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር እና የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባልነት ዋና ተደራዳሪ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር እና በኢትዮጵያ የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች ተፈራርመውታል።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ይህ ታሪካዊ ስምምነት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና የፖሊሲ ምህዳር ሙሉ በሙሉ ባስጠበቀ መልኩ የተከናወነ ነው ብለዋል።
አክለውም ስምምነቱ የሁለቱን ሀገራት የቆየ ዲፕሎማሲያዊ፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ንግድ ድርጅት ሙሉ አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ወሳኝ ስኬት መሆኑን አብራርተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም አምባሳደር ዳረን ዌልች በበኩላቸው፤ የተደረገው ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የቆየ የኢኮኖሚና የዲፕሎማሲ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።
ዩናይትድ ኪንግደም ኢትዮጵያ ወደ ዓለም ንግድ ድርጅት ለመቀላቀል የምታደርገውን ጥረት እና የምታካሂዳቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች በሙሉ ቁርጠኝነት መደገፏን የምትቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ እስካሁን ባለው ሂደት ከቻይና፣ ሩሲያ፣ አርጀንቲና፣ ቱርክ፣ ብራዚል፣ ጃፓን፣ ሕንድ፣ ኒውዚላንድ እና ታይላንድ ጋር ተመሳሳይ ስምምነቶችን ተፈራርማለች።
ዩናይትድ ኪንግደም ስምምነቱን በይፋ ከፈረሙ አባል ሀገራት 10ኛዋ እና ድርድሩን በስኬት ካጠናቀቁት ደግሞ 11ኛዋ አባል ሀገር ሆናለች።