ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ሀብቷን ለማልማት ከማንም ፈቃድ አያስፈልጋትም - የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ሀብቷን ለማልማት ከማንም ፈቃድ አያስፈልጋትም - የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የዓባይ ወንዝ ሀብቷን የመጠቀም እና የማልማት ሉዓላዊ መብት ስላላት ከማንም አካል ፈቃድ መጠየቅ እንደማያስፈልጋት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ አክለውም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለቀጣናው የሚተርፍ ሀብት መሆኑንም አመልክተዋል።
ሚኒስትሩ ከፐልስ ኦፍ አፍሪካ (The Pulse of Africa) ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የተገነባው ለኃይል ማመንጨት ብቻ እንደሆነና አዎንታዊ ሚናውን ቀጣናዊ የኤሌክትሪክ ግብይትን በማስፋት ከኢትዮጵያ ድንበር የተሻገረ ጠቀሜታ እንዳለውም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ማለትም ለጅቡቲ፣ ለኬንያ እና ለሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ እንደምትገኝ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ከሶማሊያ እና ከደቡብ ሱዳን በኩል ያለው የኢነርጂ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱንም አብራርተዋል።
የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (CFA) እና የዓባይ ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ የወንዙን የጋራ ጥቅም ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሌሎች ድንበር ተሻጋሪ የዓለም ወንዞች ላይ ባለው ተሞክሮ ትብብርን የሚጀምሩት የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ቢሆኑም፣ በዓባይ ጉዳይ ግን እንተባበር በማለት ውይይቱን በግንባር ቀደምትነት ስትመራ የቆየችው ኢትዮጵያ መሆኗን አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ በታች የሚገኙ ሊለሙ የሚችሉ መሬቶቿን ከመስኖ ልማት ውጪ ማድረጓ ለታችኞቹ የተፋሰሱ ሀገራት ያላትን ትልቅ ግምት እንደሚያሳይ ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
በቴክኒክ ደረጃ፣ ከግድቡ በታች ከ230 ሺህ ሄክታር በላይ የመስኖ ልማት የሚሆን መሬት አለን፤ ነገር ግን በታችኛው ተፋሰስ በኩል ያለውን ፍላጎት ስለምናውቅ ይህንን አላደረግነውም ሲሉ አስረድተዋል።
ሚኒስትሩ የህዳሴ ግድብ ኃይል ካመነጨ በኋላ የሚለቀቀው ውሃ ቀጥታ ወደ ታችኛው ተፋሰስ ወደሚገኙ ወንድም ሀገራት እንደሚፈስ በመግለጽ ኢትዮጵያ ለጋራ ተጠቃሚነት ያላትን ቁርጠኝነት አንስተዋል።
ሚኒስትሩ ሕዳሴ ግድብን በጋራ ለማስተዳደር የሚቀርቡ ጥሪዎችን ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ሌሎች ሀገራት በግድቡ ላይ ቁጥጥር የሚደረጉበትን አሰራርን አትቀበልም ብለዋል።
በኢትዮጵያውያን ገንዘብ የተገነባውን፣ ኩራታችን እና ብሔራዊ የክብር ፕሮጀክታችን የሆነውን ግድብ፣ ግንባታውን ሲቃወም የነበረ አካል መጥቶ በጋራ እናስተዳድር እንዴት ሊል ይችላል? ሲሉ ጠይቀዋል።
ይህ ፈጽሞ የማይቻል፣ በፍፁም ሊታሰብ የማይችል ነው ሲሉም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የኢትዮጵያን የልማት መብት ለመገደብ ከመጣር ይልቅ በውይይት እና በትብብር ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው የሚል የጸና አቋም እንዳላት ተናግረዋል።