ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ታላቅነት ማሳያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የኢትዮጵያን ታላቅነት ማሳያ ነው ሲሉ ወጣት ተመካካሪዎች ገለጹ።  

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ የቆየው ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ እየተቃረበ ይገኛል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ወጣት ተመካካሪዎች የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ የሁሉም ተመካካሪ ድምጽ የተሰማበት እንዲሁም ኢትዮጵያ የራሷን ችግሮች በራሷ እየፈታች ያለችበት ትልቅ መድረክ ነው ብለዋል።

ከተመካካሪዎቹ መካከል ወጣት ታረቀኝ በላቸው የምክክር ጉባኤ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር መሆኗ ማሳያ ነው ሲል ገልጿል።

ከሁሉም የማህበረሰቡ ክፍል የተወጣጡ ኢትዮጵያን ለጋራ መግባባት በአንድነት የተሰበሰቡበት መድረክ ነውም ብሏል።

በምክክር ሂደቱም የማያግባቡ ነገሮችን በምክክር መፍታት የሚያስችል ባህል የተገነባበት መሆኑን ነው ያስረዳው።

ይህ የምክክር ሂደትም ለአፍሪካ ሀገራት ልምድ መቅሰም የሚችሉበት ነው ሲልም ተናግሯል።

ሌላኛዋ ተመካካሪ ወጣት ገነት መለሰው የምክክር ሂደቱ አካታች በመሆኑ እንደሀገር ሀገራዊ መግባባትን በማጠናከር ዘላቂ ሰላምን የሚያረጋገጥ እንደሚሆን ያላትን ተስፋ ገልጻለች።

ምክክሩ ለሀገረ መንግስት ግንባታ በአንድነት የቆምንበት ነው ያለችው ደግሞ ሌላኛዋ ተመካካሪ ወጣት ፍቲ ሀሠን ነው።

ሁሉም ተመካካሪ ሀሳቡን በነጻነት በመሰለው መልኩ የሚገልጽበት ሁኔታ እና ለሀገራችን የሚጠቅሙ ሀሳቦች ላይ በጋራ መግባባት ላይ የደረስንበት ነውም ብላለች።

ሌላኛዋ ተመካካሪ መድሃኒት ምትኩ እንደገለጸችው ታሪካዊ እና የመጀመሪያ የሆነው ይህ ምክክር አለመግባባቶችን በምክክር መፍታት እንዳለብን የሚያስገነዝብ መድረክ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም