የአማራ ክልልን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የጸጥታ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን በላቀ ብቃት እየተወጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልልን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ የጸጥታ ኃይሎች ኃላፊነታቸውን በላቀ ብቃት እየተወጡ ነው
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፡-የአማራ ክልል የሚሊሽያና ሰላም አስከባሪ ሃይሎች የህዝቡን ሰላም በማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን በብቃት እየተወጡ መሆኑን የክልሉ ሚሊሽያ ኮሚሽን ኮሚሽነር አስቻለ አላምሬ ገለጹ።
ኮሚሽነሩ በክልሉ በጽንፈኞች ላይ የሚወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃና አጠቃላይ ሰላም በማስከበር ረገድ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም የክልሉ የሚሊሽያ እና ሌሎች የጸጥታ አካላት በቅንጅት የህዝቡን ሰላም በማስከበርና በጽንፈኞች ላይ እርምጃ በመውሰድ ህዝባዊ አደራና ኃላፊነታቸውን በላቀ ብቃት እየተወጡ ይገኛሉ ብለዋል።
በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች በዘረፋ እና እገታ ተግባር ላይ የተሰማሩ ጽንፈኞችን ተከታትሎ እርምጃ የመውሰድ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።
የጽንፈኛ ቡድኑ ዓላማ ከህገ ወጡ ህወሃት እና ሌሎችም ባንዳዎች ጋር በመሆን ታሪካዊ የውጭ ጠላቶችን እኩይ አላማ ማሳካት መሆኑን አንስተው መንግስት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ጠንካራ ህግ የማስከበር እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
የውጭ ታሪካዊ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች "ጽምዶ" በሚል በመሰባሰብ የህዝብን ሰላም ለማወክ እየጣሩ መሆኑን ያነሱት ኮሚሽነሩ የፀጥታ ሃይላችን ከህዝቡ ጋር በመተባበር ሁሌም ሰላምን ለማስከበር የላቀ ዝግጁነት ላይ ነው ብለዋል።
የክልሉን ሰላምና ፀጥታ በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የህዝቡ ድጋፍ፣ ትብብርና እገዛ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።