ቀጥታ፡

በመዲናዋ የተገነቡ የመዝናኛ ፓርኮች አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ከዘመናዊ የቱሪዝም መስህቦች ጋር አስተሳስራ እንድትቀጥል አስችለዋታል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦በመደመር መንግሥት በመዲናዋ የተገነቡት የመዝናኛ ፓርኮች አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ከዘመናዊ የቱሪዝም መስህቦች ጋር አስተሳስራ እንድትቀጥል ማስቻላቸውን የአንድነት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

በመዲናዋ የተገነቡት ፓርኮች ልዩ ልዩ ሁነቶችን ማከናወን የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች የተሟላላቸው እና ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ማስቻላቸውም ተመላክቷል።

የመደመር መንግሥት ቱሪዝምን አንዱ የኢኮኖሚ ምሰሶ በማድረግ በገበታ ለሸገር፣ ገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ተነሳሽነቶች አማካኝነት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ዘመናዊ የቱሪስት መዳረሻዎችን ገንብቷል።

እነዚህ ግዙፍ የቱሪዝም መዳረሻ የልማት ሥራዎች የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ኢትዮጵያን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ በማድረግ ከዘርፉ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ አስችለዋታል።

በገበታ ለሸገር ከተገነቡት የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል የአንድነት ፓርክ  የመዲናዋን ማራኪነት በማጎልበት በጎብኚዎች ተመራጭ እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል።

ወዳጅነት ፓርክ አንድ እና ሁለት አዲስ አበባ የዲፕሎማሲ ገጽታዋን ከዘመናዊ ቱሪዝም ጋር አጣጥማ እንድታስቀጥል ምቹ ዕድል ፈጥረዋል።

የአንድነት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ነጃት ግርማ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ፓርኮቹ ባለፉት ዓመታት በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ጎብኚዎችን መሳብ ችለዋል።

የፓርኮቹ ተገንብቶ አገልግሎት መስጠት ለበርካታ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠራቸውንም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ፓርኮቹ የተለያዩ ሁነቶችን በማስተናገድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር ማስቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡

ይዘት ፈጣሪዎች ሥራዎቻቸውን የሚያከናውኑበት ተመራጭ ማዕከል መሆን መቻላቸውን ጠቅሰው፤ የተለያዩ የንግድ ተቋማት በፓርኩ ሥራቸውን በተሻለና ምቹ በሆነ መልኩ እንዲያከናወኑ ማድረጉን ተናግረዋል።

ይህም የኢኮኖሚ ፍሰቱን በማሳለጥ በኩል አወንታዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በፓርኩ ሲዝናኑ ያገኘናቸው ወጣቶች በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት የሚደነቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ 


 

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ናሆም ተስፋዬ፣ በአሁኑ ወቅት የአንድነት ፓርክን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶች መገንባታቸው በርካታ ጠቀሜታ እንዳላቸው ተናግሯል፡፡ 

ይህም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች መሳብ እንዲሁም የኢትዮጵያን ገጽታ በመገንባት በኩል አበርክቷቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

በመዲናዋ የተገነቡ እና እየተገነቡ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ስፍራዎች ለከተማዋ የቱሪዝም ዘርፍ መነቃቃት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ቤዛ ክፍሌ ናት፡፡ 


 

በከተማዋ የተገነባው የአንድነት ፓርክም ለጎብኚዎች ምቹ እና ተመራጭ የመዝናኛ ስፍራ ከመሆን ባለፈ ለቱሪዝም እድገት የራሱን ከፍተኛ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጻለች፡፡ 


 

ሌላው አስተያየት ሰጪ ወጣት ሀንደሰ ዓለሙ በበኩሉ፣ አንድነት ፓርክ ለወጣቶች የስራ ትስስር እና የሀሳብና ልምዶችን የሚጋሩበት ምቹ አውድ መፍጠሩን ገልጿል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም