ቀጥታ፡

በሐረሪ ክልል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን የመከላከል እና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ

ሐረር፤ ነሐሴ 14/ 2018 (ኢዜአ)፦ በሐረሪ ክልል በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የሚከሰቱ አደጋዎችን የመከላከል፣ የመቀነስ እና ፈጣን ምላሽ የመስጠት ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።

የሐረሪ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር እና ማኅበረሰብ አቀፍ እንክብካቤ ጥምረት ምክር ቤት በክልሉ የሚከሰቱ አደጋዎችን የመከላከል፣ የመቀነስ እና ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን ለማጠናከር ያለመ መደበኛ ስብሰባውን አካሂዷል።


 

ምክር ቤቱ በ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ በ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ፣ በቀጣይ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰፊው ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ወይዘሮ ሮዛ ኡመር በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ለአደጋዎች የማይበገር ማኅበረሰብን ለመገንባት አደጋዎች ከመከሰታቸው በፊት የመከላከልና የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎች ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል።

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመከላከልና ለመቀነስ የማኅበረሰቡንና የባለድርሻ አካላትን የተቀናጀ ጥረት ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

በተለይም በክልሉ ከዝናብ እጥረት ጋር ተያይዞ ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳቶችን ለመከላከልና ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት ቅነሳ ለማካካስ የሚያስችሉ የተቀናጁ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

የዝናብ እጥረት ጫና በግብርና፣ በውሃ አቅርቦትና በሌሎች ዘርፎች ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

በራስ አቅም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የመስኖ ልማትን ማጠናከር፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ፣ የምርት ክምችትን ማጠናከር እና የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ከዝናብ ጥገኝነት ማላቀቅ እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የክረምቱ ዝናብ ሁኔታ የሰብል እጥረት ሊያስከትል ስለሚችል፣ አርሶ አደሮች የሚገኘውን እርጥበት በአግባቡ የማቆር ሥራዎችን በልዩ ትኩረት ሊያከናውኑ እንደሚገባ መክረዋል።

በተጨማሪም እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህልን ማጠናከር፣ ሁሉንም የሀብት አሰባሰብ አማራጮች መጠቀም እና ድጋፎችን ተቋማዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ምርታማነትን የሚጨምሩ አሰራሮችን ከመከተል ባሻገር ድርቅን የሚቋቋሙና በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የሰብል ዝርያዎችን መዝራት፣ ለከብቶች መኖ ማከማቸት እንዲሁም ውሃ ማጠራቀምን የመሰሉ የጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢና አስፈላጊ ነው ብለዋል።

በውይይቱ የውሃ አጠቃቀምን በማሻሻል፣ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት እና ፈጣን የእርሻ ድጋፎችን በማቅረብ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ አቅጣጫዎች ተቀምጠዋል።

ምክር ቤቱ የሰብአዊ ድጋፍ ሥራዎችን በራስ አቅም ለማስፈጸም የሚያስችል የበጀት ሰነድ እና የአደጋ ስጋት ምላሽ ፈንድ የሀብት አሰባሰብ ረቂቅ መመሪያ ላይ በጥልቀት በመወያየት አጽድቋል።

የምክር ቤቱ አባላትም በአደጋ ስጋት ቅነሳ እና ምላሽ አሰጣጥ ሂደት ላይ የሚታዩ ማነቆዎችን በመቅረፍ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

አደጋዎች በሚከሰቱበት ወቅት ፈጣን ምላሽ ሰጪ ስርዓት በመዘርጋትና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የተቀመጡ የቅድመ ጥንቃቄ ውሳኔዎችን ወደ ተግባር ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም