የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት የተከናወነው ተግባር ውጤታማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት የተከናወነው ተግባር ውጤታማ ነው
ደሴ፤ ነሐሴ 14/2018(ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት የተከናወነው ተግባር ውጤታማ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ሪጅን ገለጸ።
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ሀብቱ አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን በማስፋት የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በቅንጅት የተሠራው ሥራ ውጤታማ ነው።
በዚህም በደሴ፣ በደቡብ ወሎ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በኮምቦልቻና አካባቢዋ 29 ሺህ 191 አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የተከናወነው ተግባር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ9 ሺህ ደንበኞች ብልጫ እንዳለው የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ ይህም በቅንጅትና በትብብር በመሥራት የመጣ ውጤት መሆኑን አስረድተዋል።
በአዲሱ በጀት ዓመትም ከ43 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ኅብረተሰቡም በአካባቢው የሚገኙ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን፣ መስመሮችን፣ ትራንስፎርመሮችንና ሌሎች የመሠረተ ልማት አውታሮችን በንቃት እንዲጠብቅም አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የደሴ ሪጅን ከ250 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት ከሪጅኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።