በሰሜን ጎጃም ዞን 118 ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል-መምሪያው - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ጎጃም ዞን 118 ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎች ተገንብተዋል-መምሪያው
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 14/2018(ኢዜአ)፡-በሰሜን ጎጃም ዞን 118 ደረጃቸውን የጠበቁ የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባት ለመጪው የትምህርት ዘመን ዝግጁ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ትምህርት መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ኃላፊ አቶ ነጋልኝ ተገኘ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በአዲሱ የትምህርት ዘመን በተለያዩ የትምህርት ደረጃዎች 479 ሺህ 781 ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የሚያስችል የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተከናውኗል።
ባለፉት ጊዜያት በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የተፈጠረውን ጫና ለማቃለል ማኅበረሰቡን በባለቤትነት በማሳተፍ የዝግጅት ሥራ እየተካሄደ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
በትምህርት ዘመኑ በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋለውን የመማሪያ ክፍል ጥበት ለመፍታት በተደረገው ጥረት ውጤታማ ሥራ ማከናወን መቻሉንም ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥም 118 ደረጃቸውን የጠበቁ አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባት ለመጪው የትምህርት ዘመን ዝግጁ ማድረግ እንተደቻለ ነው ያስታወቁት
በተጨማሪም 12 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን በጠበቀ አግባብ እየተገነቡ ሲሆን፣ እስከ መስከረም 30 ቀን 2019 ዓ.ም. ድረስ ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን ለመገንባት ከኅብረተሰቡና ከአጋር አካላት ከ327 ሚሊዮን ብር በላይ ሀብት ማሰባሰብ እንደተቻለም አስገንዝበዋል።
የተማሪዎች መደበኛ ምዝገባ ከነሐሴ 18 እስከ ጳጉሜ 5ቀን 2018 ዓ.ም. የሚካሄድ ሲሆን፤ በዚሁ ጊዜ ውስጥ ማኅበረሰቡ ለትምህርት የደረሱ ሕፃናትን በማስመዝገብ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
በትምህርት ዘመኑ በመማሪያ ቁሳቁስ እጥረት ምክንያት ዜጎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይሆኑ ለማድረግም ከ25 ሺህ ደርዘን በላይ ደብተርና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን መሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
በዚህ የትምህርት ዘመን ከቅድመ አንደኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚገኙ 520 የሚጠጉ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራው መዘጋጀታቸውንም ኃላፊው አስታውቀዋል።