በሐረሪ ክልል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመደመር መንግሥት እሳቤን በተግባር ባንፀባረቀ መልኩ እየተተገበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሐረሪ ክልል የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የመደመር መንግሥት እሳቤን በተግባር ባንፀባረቀ መልኩ እየተተገበረ ነው
የመደመር እሳቤ የትብብር፣ የመተማመን፣ የአንድነትና የጋራ ኃላፊነት መርህን በማጠናከር የሀገር ግንባታን ለማፋጠን የሚያበረታታ ነው።
መደመር የልዩነትን ኃይል ወደ ጋራ ጥቅም የሚቀይር እሳቤ እንደሆነው ሁሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትም ይህንን ፍልስፍና በተግባር ያንጸባርቃል።
ዜጎች ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በማዋሃድ የማኅበረሰብን ችግሮች በጋራ ሲፈቱ የአንድነት መንፈስ ይጠናከራል፣ የመተማመን ባህልም ይጎለብታል።
በመደመር መንግሥት ዘመን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከግለሰብ ተሳትፎ ባለፈ የሀገራዊ እንቅስቃሴ መልክ ይዞ እየተከናወነ ይገኛል።
በዚህ ረገድም መርሃ ግብሩ በሐረሪ ክልል የመደመርን ፍልስፍና በተግባር ከሚያንፀባርቅ መልኩ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
በዚህም በክልሉ ባለፉት ዓመታት የሰው ተኮር ስራዎችና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በተከናወኑ ተግባራት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።
ለአብነትም ባለፉት አምስት ዓመታት በክረምት የበጎ ፍቃድ መርሐ ግብሮች በክልሉ ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የአቅመ ደካሞች ቤት መገንባትና የማደስ ሥራዎች፣ የትምህርት ቤቶችን፣ የጤና ተቋማት እድሳት ስራዎች ይጠቀሳሉ።
በተጨማሪም በዚሁ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በሚሊዮን የሚቆጠር ችግኞች ከመተከላቸውም ባሻገር የነፃ ህክምና አገልግሎት፣ የአካባቢ ጽዳትና የቆሻሻ ማስወገድ ሥራዎች በበጎ ፍቃደኞች ተከናውነዋል።
ለአረጋውያን፣ ለአካል ጉዳተኞች ማዕድ ማጋራት፣ የአልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ እንዲሁም የደም ልገሳ ተግባርም በሰፊው ሲከናወን ቆይቷል።
ለተማሪዎችና ለትምህርት ቤቶች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ፣ የትምህርት ቤት ግንባታና እድሳትና የቤተ መጻሕፍት ማደራጀት የመሳሰሉ ተግባራት በጎ ፈቃደኞች ተከናውነዋል።
ይህ የበጎ ፍቃድ ባህል በያዝነው የክረምት ወራት በ14 የተለያዩ አገልግሎቶች ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ይህም ዘላቂ ልማት፣ ለማህበራዊ አንድነትና ለሀገራዊ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
የሐረሪ ክልል መንግሥት በመደመር መንግሥት ሰው ተኮርነትን የእሳቤዎቹ ምሰሶ በማድረግ የጀመራቸውን ስኬታማ ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።