ቀጥታ፡

የሙዝ ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነቱን ለማሳደግ የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የሙዝ ምርትን በዓለም አቀፍ ገበያ ያለውን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የጥራት ማሻሻያና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ አበባ፣ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር የሙዝ ወጪ ንግድ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ጉባዔ እያካሄደ ይገኛል፡፡


 

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሙዝ ምርት መጠን ቢኖርም ለውጭ ንግድ የሚቀርበው ለጎረቤት ሀገራት ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ ያላትን ለግብርና የተመቹ አግሮ-ኢኮሎጂያዊ ሁኔታዎች ወደ ሀብትና ካፒታል በመቀየር ዓለም አቀፍ የገበያ መዳረሻዎችን ማስፋት ይገባል ብለዋል።

የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብር በሆርቲካልቸር ዘርፍ ስኬቶች እንዲመዘገቡ ማድረጉን በማንሳት፤ በአትክልትና ፍራፍሬ ያለውን ተቋማዊ ልምድ፣ የሎጂስቲክስ እውቀት እና ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የግብርና ሚኒስቴር ዘርፉን ገበያ ተኮር፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገርና ዘላቂ ለማድረግ በርካታ የፖሊሲ እና የስትራቴጂ ማዕቀፎችን ቀርጿል ብለዋል።

የኢትዮጵያን ሆርቲካልቸር ዘርፍ ለማሳደግ የ10 ዓመት ብሔራዊ የሆርቲካልቸር ስትራቴጂ በመቅረጽ ለዘርፉ እድገት በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የሙዝ ምርት ዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነትን ለማሳደግ የጥራት ማሻሻያና የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በአበባና በአትክልት ዘርፍ የተገነባው ተቋማዊ ልምድ፣ የሎጂስቲክስ እውቀት እና ዓለም አቀፍ የገበያ ትስስር ለሙዝ ኢንዱስትሪው ስኬት መጠቀም ይገባልም ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ አበባ አትክልትና ፍራፍሬ አምራች ላኪዎች ማህበር ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ ዘውዴ፤ በሆርቲካልቸር ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም ለመጠቀም ከግብርና ሚኒስቴር እና ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዛት ከሚመረቱ የፍራፍሬ ዝርያዎች አንዱ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ከምግብነት ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የገቢ ምንጭና ሥራ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም