ቀጥታ፡

ህዝበ ሙስሊሙ መውሊድን ሲያከብር የበዓሉን እሴቶች በመጠበቅና በመረዳዳት ሊሆን ይገባል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ ህዝበ ሙስሊሙ መውሊድን እሴቶቹን በመጠበቅ እርስ በእርስ በመረዳዳትና ለአቅመ ደካሞች በመድረስ ሊያከብረው እንደሚገባ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ።

ዘንድሮ የሚከበረው 1 ሺህ 501ኛው የመውሊድ በዓል በተለያዩ ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ኹነቶች እንደሚከበር ጠቅላይ ምክር ቤቱ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።


 

የአንዋር መስጊድ ኢማም እና ኸጢብ፣ እንዲሁም የመውሊድ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሼህ ጧሃ መሐመድ ሃሩን እንደገለጹት፤ መውሊድ የነቢዩ ሙሐመድን አርአያነት እንድንከተልና እውቀት እንድንቀስም ያስችላል።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት የዑለማዎች ጉባኤ አባል ሼህ መህሙድ ከሪም በበኩላቸው፤ ሕዝበ ሙስሊሙ መውሊድን ሲያከብር የነቢዩ ሙሐመድን አስተምህሮ በመከተል አቅመ ደካሞችንና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በማገዝ እንዲሁም ለሀገር ሰላም ዱዓ በማድረግ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ሸሪፍ ሀሰን በበኩላቸው፣ የዘንድሮውን የመውሊድ በዓል ልዩ የሚያደርገው በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙስሊሞች መሪያቸውን በመረጡበትና ሕገ-መጅሊስ አዋቅረው ባጸደቁበት ማግስት መከበሩ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ምክር ቤቱ ሕዝበ ሙስሊሙ የበዓሉን እሴቶች በመጠበቅ እርስ በእርስ በመረዳዳትና ለአቅመ ደካሞች በመድረስ በዓሉን በሰላምና በፍቅር እንዲያከብር በማስገንዘብ መልካም ምኞቱን አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም