ቀጥታ፡

ጉባኤው ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ሀሳብ እንድናዋጣ ዕድል ፈጥሮልናል - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሁላችንም ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ሀሳብ እንድናዋጣ ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ ቆይቶ ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ እየተቃረበ ይገኛል።

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ተመካካሪዎች መካከል ወጣት መርቀኒያ አሊ፣ ጉባኤው እጅግ ስኬታማ፣ አሳታፊ እና እውነተኛ ኢትዮጵያዊነት የታየበት መሆኑን ተናግራለች።

የምክክር ጉባኤው ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሃሳብ ለመለዋወጥ ትልቅ ዕድል መፍጠሩን ጠቁማ፤ የምክክር ሂደቱ በመደማመጥ ለሀገር ግንባታ ሂደቱ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የበሰሉ ሀሳቦች የመነጩበት ትልቅ ዕድል ነው ብላለች።

መሰል ሀገራዊ የምክክር ሂደት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ከተደረገ የበለጸገችና ታላቅ ሀገር ለመገንባት ጥሩ መደላድል እንደሚፈጥርም ነው የገለጸችው።

ይህ ታሪካዊ ሀገራዊ የምክክር ሂደት እስካሁን ለቆዩት ችግሮች የጋራ መፍትሔ ከመስጠት ባለፈ ቀጣዩ ትውልድ ምክክርን ባህል እንዲያደርግ ጠንካራ መሰረት ጥሎ እንደሚያልፍ ተናግራለች።

ሌላኛው ተመካካሪ ተረፈ ተከራይ በበኩሉ ሀገራዊ ምክክሩ ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ሀሳብ እንድናዋጣ ዕድል ፈጥሮልናል ሲሉ ገልጸዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ቀደም ሲል በሀገሪቱ ለአለመግባባት መንስኤ የነበሩ ጉዳዮችን በጥልቀት ለመመርመር ዕድል የሰጠ ታሪክዊ ጉባኤ ነው ብለዋል።

የምክክር ሂደቱ እኩል ሀሳብ የመስጠት ዕድል የተረጋገጠበትና አሳታፊ እንደነበርም ተናግረዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው ሀገርን ወደፊት የሚያራምዱና ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ግብዓት የሚሆኑ በሳል ሀሳቦች የተንሸራሸሩበት መሆኑን አብራርተዋል።

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው መደማመጥ ላይ የተመሰረተ የሀሳብ መዋጮ የተስተናገደበት በመሆኑ ለሀገር ለዘላቂ ሰላምና አንድነት መጠናከር መሰረት የሚጥል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ተመካካሪ ወይዘሮ ሃሊማ ሰይድ ናቸው።

ጉባኤው ተመካካሪዎች የአንዱን ችግር እንደራሳቸው እንዲመለከቱ ዕድል በመፍጠር በጋራ የመፍትሔ ሀሳቦች የተመላከቱበት ጉባኤ እንደሆነ ገልጸዋል። 

ሀገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚያመጣና የጋራ መግባባትን የሚያጎለብት መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም