በኦሮሚያ ክልል ከ18 ሺህ 800 ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል ከ18 ሺህ 800 ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል
አዳማ ፤ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ከ18 ሺህ 800 ካሬ ሜትር በላይ የከተማ መሬት ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ መደረጉን የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ።
የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አብደላ ኦገቴ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለያዩ ሴክተሮች ሙስና እና ብልሹ አሰራሮችን ለመከላከል የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን አንስተዋል።
በክልሉ በመንግስት ተቋማት የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያስችሉ 26 የሙስና መከላከል የአሰራር ስርዓት ጥናቶች መካሄዳቸውን ዘርዝረዋል።
የመስኖ ፕሮጀክት ግንባታና የውል አስተዳደር፣ የሕገ-ወጥ ንግድ ክትትል እና የገቢ አሰባሰብ ስርዓት፣ የግል ህክምና ተቋማት የፈቃድ አሰጣጥና ክትትል፣ የአርሶ አደሮች ህብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒየኖች የግዥና ሽያጭ አሰራር ጥናቶች የሚገኙበት መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም በመሬት ሃብት ላይ የሚደርሰውን ምዝብራ ለመከላከል ብዙ ጥረት መደረጉን አስታውሰው፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 18 ሺህ 849 ካሬ ሜትር የከተማ መሬት ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ ተደርጓል ብለዋል።
በዚህም የከተማ መሬትን ከህገ-ወጥ ወረራ፣ ከደላሎች ድብቅ ሽያጭ እና ከአሰራር ብልሹነት በመታደግ ወደ "መሬት ባንክ" ማስገባት፤ መሬቱ ለታለመለት ልማት እንዲውል ማድረግ እየተቻለ ስለመሆኑ አንስተዋል።
በተጨማሪም በየደረጃው ለሚገኙ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታቅዶ፤ ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት ተደራሽ በማድረግ ከእቅድ በላይ ማሳካት ስለመቻሉ ተናግረዋል።
የሙስና ወንጀል ህጎች፣ የግዥና ግንባታ አስተዳደር ውል ህጎች፣ የሀብት ማስመለስ አዋጅ፣ የሙያ እና የአመራርነት ሥነ-ምግባር እንዲሁም የመከላከል ስትራቴጂዎች ላይ በማተኮር ግንዛቤ ስለመሰጠቱም አስታውሰዋል።
ከ135 ሺህ በላይ የህዝብ ተመራጮች፣ ተሿሚዎች እና የመንግስት ሰራተኞች በዲጂታል ቴክኖሎጂ የታገዘ የሃብት ምዝገባ ስራ ስለመካሄዱም ገልጸው በተያዘው ዓመትም መሰል ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
በሀገሪቷ በወጣው የሀብት ማስታወቂያና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሠረት ተሿሚዎችና የመንግስት ሰራተኞች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚደነግግ መሆኑ ይታወቃል።