የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለአህጉራዊ ውድድሮች ብቁ መሆኑ ከስፖርቱ ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለአህጉራዊ ውድድሮች ብቁ መሆኑ ከስፖርቱ ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው
ባህር ዳር፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለአህጉራዊ ውድድሮች ብቁ መሆኑ ከስፖርት ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።
የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ለአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች ዝግጁ ለማድረግ ሰፊ የማሻሻያና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው ይታወቃል።
የስታዲየሙን ለጨዋታ ዝግጁ መሆን ከውድድር ባለፈ በተለይም ለቱሪዝም ያለውን ፋይዳ በተመለከተ የአማራ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አየለ አናውጤ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም የባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ለአህጉራዊ ውድድሮች ብቁ መሆኑ ከስፖርትም ባለፈ ለቱሪዝም ዘርፍ ማንሰራራት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን አስረድተዋል።
ከእግር ኳስ ውጭም በከተማዋ የውሃ ዋና፣ የአትሌቲክስ እና የብስክሌት ውድድሮችን ለማስፋት ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ነው የጠቆሙት ።
በከተማዋ የተገነቡ እና በመገንባት ላይ ያሉ ባለ ኮከብ ሆቴሎች መኖራቸው የካፍ ባለሙያዎችን መስፈርት የሚያሟላ እና ለዘርፉ ዘላቂ እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም የስታዲየሙ ዝግጁነት ለሀገራዊ የስፖርት እድገት እንዲሁም ለስፖርት ቤተሰቡ እና ለብሔራዊ ቡድኑ ጭምር ትልቅ የምስራች መሆኑን ጠቅሰው ለቱሪዝም ዘርፉም ትልቅ አቅም ይሆናል ብለዋል።
ስታዲየሙ የጨዋታ መስፈርቱን አሟልቶና ብቁ ሆኖ መገኘቱ ብሔራዊ ቡድኑ እና ክለቦች አህጉራዊ ጨዋታዎችን በሜዳቸውና በደጋፊዎቻቸው ፊት የመጫወት ዕድል አመቻችቷል።