ቀጥታ፡

የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስርዓት የባለስልጣኑን የአገልግሎት አሰጣጥ አቀላጥፏል

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓት ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሰጥ ማስቻሉን የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ጌታቸው (ዶ/ር) ገለጹ።

ይህ የተቀናጀ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥ የተገልጋዮችን እርካታ በማሳደግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ተናግረዋል።

መንግስት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ በማድረግ ቀልጣፋና ግልጽ አገልግሎት ለመስጠት ዲጂታል 2025 ስትራቴጂን በውጤታማነት በመተግበር ሀገሪቱ ዲጂታል 2030 ስትራቴጂን ነድፋ እየተገበረች ትገኛለች።

በዚህ መነሻ እየተተገበረ ያለው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተበታተኑ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከልና በተቀናጀ አግባብ እንዲመሩ በማድረግ የተገልጋዮችን እርካታ እያሳደገ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሰለሞን ጌታቸው (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት ባለስልጣኑ ከኢትዮጵያ ጉምሩክ ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎች ቁጥጥር አገልግሎትን በአንድ መስኮት እየሰጠ ይገኛል።

ይህ አሰራር አገልግሎት አሰጣጡን በማቀላጠፍ የተገልጋዮችን እርካታ እያሳደገ መሆኑን ገልጸው፤ ይህን የበለጠ ለማላቅ አገልግሎቶቹን በቴክኖሎጂ የማስደገፉን ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በዚህም መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ውስጥ የሚገቡ 48 አገልግሎቶች መለየታቸውንና በሂደቱ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

እነዚህ አገልግሎቶች የባለስልጣኑን የአገልግሎት ተደራሽነት ከማስፋት ባሻገር ጥራትና ቅልጥፍናን በማሳደግ የተገልጋዮችን እርካታ የበለጠ እንደሚያሳድጉም አክለዋል።

ባለስልጣኑ አሁን ላይ ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ባገኘው ቴክኖሎጂ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎች ላይ ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም የህግ መተላለፎች ሲከሰቱ ምዝገባ፣ ትንተና እና ሌሎች ተገልጋይ ተኮር ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂው ባለስልጣኑ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ግልጽ እና ቀልጣፋ በማድረግ የተገልጋዮችን እርካታ እያሳደገ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ይህን የተገልጋዮች የአገልግሎት እርካታ የበለጠ ለማሳደግ አገልግሎቶቹን ወደ መሶብ የአንድ ማዕከል ማስገባት የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም