ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ እና ሩሲያ በሰው ሃይል ልማትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ በጋራ ይሰራሉ - በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ) ፦ በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ያለውን ትብብር በማጠናከር በምርምር፣ በሰው ሃይል ልማት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር በጋራ እንደሚሰሩ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴርኪን ገለጹ።

አምባሳደሩ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን ጎብኝተዋል።


 

በጉብኝታቸው ወቅትም አምባሳደሩ አንደተናገሩት በኢትዮጵያ እና በሩሲያ መካከል ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ጠንካራ የሁለትዮሽ ግንኙነት አለ።

ይሄንን ግንኙነት መሰረት በማድረግም ሁለቱ ሀገራት በምርምር ፣ በሰው ሃይል ልማት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር በጋራ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

ይህ የሁለቱ ሀገራት አጋርነት የብሪክስ አባል ሀገራት አርቲፊሻል ኢንተለጀንስን ለጋራ ዕድገትና ተጠቃሚነት ለማዋል ከሚያደርጉት ሰፊ ጥረት ጋር የሚጣጣም መሆኑም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ኢንስቲትዩቱ በሀገሪቱ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውስጥ እያከናወናቸው ያሉ ወሳኝ ስራዎችን አስመልክተው ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገዋል።


 

በዚህም ኢንስቲትዩቱ የሚያከናውናቸው የምርምርና የልማት ስራዎች በኢትዮጵያ ቅድሚያ በተሰጣቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ እምርታ እንዲመዘገብ ማስቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም