ቀጥታ፡

የምክክር ጉባኤው ሀገራዊ የምክክር ባህልን በማዳበር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፦ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ የምክክር ባህልን በማዳበር የተሻለች ኢትዮጵያን ለመገንባት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ነው ሲሉ ተመካካሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዋናው ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሲካሄድ ቆይቶ ወደ ማጠቃለያው ምዕራፍ እየተቃረበ ይገኛል።

ተመካካሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ምክክሩ የሀገሪቱን ዘለቂ ሰላም፣ አንድነትና ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ መሠረት የሚጥል ነው።

ምክክሩ በልዩነቶች መካከል የጋራ መግባባትን ለመፍጠር እና የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት አዲስ ምዕራፍ መክፈቱንም አስታውቀዋል።

ተመካካሪ ካፒቴን ሰለሞን ግዛው እንደገለጹት፣ ምክክሩ የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላምና እድገት በጽኑ መሠረት ላይ ለመጣል የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

ይህም ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ታላቅ ዕድል መሆኑን አስታውቀዋል።

በምክክሩ ወቅት የላቀ የመተሳሰብና የሌሎችን ችግር እንደ ራስ የማየት ሂደት መታየቱን የጠቆሙት ካፒቴን ሰለሞን፣ የቡድን አደረጃጀቱም ሀሳብን በነፃነት ለማንሸራሸር ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል።


 

ሌላኛዋ ተመካካሪ ወይዘሮ ሰላም ዋቆ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ምክክሩ ችግሮችን በምክክር መፍትሔ ማበጀት እንደሚቻል በተግባር የተረጋገጠበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

በምክክር ሂደቱ የሁሉም ተሳታፊዎች ሀሳብ ያለ ምንም ልዩነት በእኩልነት የተደመጠበት፣ የጋራ መከባበርና መግባባት የሰፈነበት እንደሆነም አብራርተዋል።

ምክክሩ ከሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎችና ከውጭ ሀገራት የተውጣጡ ኢትዮጵያውያን በአንድ ጥላ ስር ተሰባስበው ሀገራቸውን ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር የመከሩበት ታሪካዊ መድረክ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሻለቃ ባሻ ተረፈ ወላኒ ናቸው።


 

የምክክር ሂደቱ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ያሳተፈና አካታች እንደነበር ያነሱት ሻለቃ ባሻ ተረፈ፣ መድረኩ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም፣ ወንድማማችነትና ሀገራዊ አንድነት እንዲጸና ለማድረግ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አብራርተዋል።

በምክክሩ ወቅት የታየው የመደማመጥና የመመካከር በጎ ልምድ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ሀገራዊ የፖለቲካና የማህበራዊ ባህል ሆኖ በዘላቂነት ሊቀጥል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም