የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ዘላቂ ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ አስችሎናል-አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ዘላቂ ተጠቃሚነታችንን ለማረጋገጥ አስችሎናል-አርሶ አደሮች
ደብረብርሃን፤ ነሀሴ 14/2018 (ኢዜአ)፡-በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በመሳተፍ ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ መቻላቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የቤተሰብንና የሀገርን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ የስነ-ምግብ አቅርቦትን ለማሻሻል እና የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት ተግባራዊ የተደረገ ወሳኝ ሀገራዊ ንቅናቄ ነው።
መርሃ ግብሩ በዋናነት የእንስሳት እና የዶሮ እርባታን፣ የወተት ምርትን፣ የ ማር እና የዓሣ ሀብት ልማትን በማስፋፋት አነስተኛ የቤት ውስጥ ምርታማነትን ወደ ላቀ የገበያ መር ምርት ማሸጋገርን ዓላማ ያደርጋል።
በደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር የባቄሎ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሰለሞን ሽፈራው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለወተት ልማት ዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ በተሻለ መንገድ ተጠቃሚ ለመሆን አስችሎናል።
በተለይም ዝርያቸው የተሻሸሉ የወተት ላሞችን በማራባት ዘላቂ ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ እንደቻሉ ነው የሚናገሩት።
በተለይ የእንስሳት መኖ አቅርቦትና የአመጋገብ ሥርዓቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ ከአንድ ላም በቀን በአማካይ 20 ሊትር ወተት ማግኘት ማስቻሉን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት በቀን ከ50 ሊትር በላይ ወተት ለሕብረት ሥራ ማህበራቸው በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
በዚህም መኖሪያ ቤታቸውን ከማዘመን ባለፈ ገንዘብ ለመቆጠብና ሀብት ለማፍራት እንደቻሉ ገልጸዋል።
በተመሳሳይ በከተማ አስተዳደሩ የወሻውሽኝ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ጌታሁን ገነነ በበኩላቸው፣ ቀደም ሲል ከነበሯቸው የሀገር ውስጥ ላሞች በቀን ከአራት ሊትር ያልበለጠ የወተት ምርት ያገኙ እንደነበር አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን የላሞችን ዝርያ በማሻሻል፣ በቂ መኖ በማዘጋጀትና የአመጋገብ ሥርዓቱን በማዘመን ከአንድ ላም በቀን እስከ 20 ሊትር ወተት ለማግኝት መቻላቸውን አስረድተዋል።
የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የእንስሳትና እንስሳት ተዋጽኦ ግብይት ቡድን መሪ አቶ ዳዊት አሳምነው በበኩላቸው፣ በበጀት ዓመቱ 37 ሚሊዮን 100 ሺህ ሊትር ወተት ለ44 አቀነባባሪዎች ማቅረብ መቻሉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው የወተትና የወተት ተዋጽኦ ምርት ግብይት በመፈጸም አምራቾችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።
የተገኘውንም ውጤት በአዲሱ የበጀት ዓመት በማስፋት አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።