ቀጥታ፡

ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን ያሰፈነች ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት የሚያስችል ሐሳብ እንደሚገኝበት ተስፋ እናደርጋለን-የሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች

ሰመራ፣ነሀሴ 14/2018 (ኢዜአ)፡-ሃገራዊ ምክክሩ ዘላቂ ሰላምን ያሰፈነች ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት የሚያስችል ሐሳብ እንደሚገኝበት ተስፋ እናደርጋለን ሲሉ የሎጊያ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ዘመናትን ያስቆጠሩ ችግሮቻችንን በውይይት ለመፍታት ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ እየተካሄደ ያለው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ወደ ማጠቃለያ ምዕራፍ እየተቃረበ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ ከመላው የሀገራችን ክፍሎችና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ተወካዮችን ጨምሮ አራት ሺህ ተሳታፊዎች የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ በስምንት አጀንዳዎች ላይ በንቃት ሲሳተፉ ቆይተዋል።

ምክክሩ በዋናነት ዓላማ አድርጎ የተነሳው በሀገራዊ የጋራ ፍላጎቶችና በመሠረታዊ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን በማሳደግ፣ ግጭቶችን ማስቀረትና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር ነው።

በዚህ ዙሪያ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሎጊያ ከተማ ነዋሪዎችም ዘላቂ ሰላምን ያሰፈነች ጠንካራ ሀገርን ለመገንባት የሚያስችል ሐሳብ እንደሚገኝበት ተስፋ እናደርጋለን ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል አቶ መንደል ዓሊ እንደገለፁት፤ በመወያየት የማይፈታ ችግር የለም፤ የአፋር ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓትም ለምክክር ሰፊ ቦታ የሚሰጥ ነው። 

ምክክሩ በመነጋገር አለመግባባቶችን በጋራ መፍታት እንደሚቻል በተግባር ያረጋገጠና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት፣ አንድነቷ የጠነከረ ኢትዮጵያን ለመገንባት ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። 

እንዲሁም ምክክሩ የተሻለና ለሀገር አንድነት የሚጠቅም ሐሳብ ይገኝበታል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው፣ ምክክሩ ለኢትዮጵያውያን ብሩህ ተስፋ የሰነቀ መሆኑን ገልጸው 

ለረጅም ጊዜ መፍትሔ አጥተው ለቆዩ ችግሮችም መፍትሔ እንደሚያመጣ ተስፋ እንዳላቸው አስረድተዋል። 

ሰላምና ልማትን በላቀ ሁኔታ ለማረጋገጥ ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ሚና እንዳለው የተናገሩት ደግሞ አቶ አስራት ገብረሥላሴ ናቸው። 

በምክክሩ የቀረቡት አጀንዳዎች የጋራ መገለጫዎቻችንና ሳይፈቱ የቆዩ ችግሮችን ለመፍታት መንገዱን ያመቻቹ፣ ሰላምና አንድነትን ለማምጣትም ወሳኝ በመሆናቸው በሂደቱ ላይ ተስፋን እንድንሰንቅ አድርጎናል ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም