ቀጥታ፡

በወልዲያ ከተማ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ11 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል- መምሪያው

ወልዲያ፤ ነሐሴ 14/2018 (ኢዜአ)፡- በወልዲያ ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለ11 ሺህ 768 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የከተማ አስተዳደሩ ሥራና ክህሎት መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ መላኩ አለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የከተማዋን ሰላም ከማረጋገጥ ጎን ለጎን ለወጣቶች የሥራ ዕድል የመፍጠር ተግባር ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ለ9 ሺህ 268 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣  ከእቅድ በላይ  ለ11 ሺህ 768 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ተችሏል።

ይህም ከዕቅዱ ጋር ሲነጻጸር 127 በመቶ አፈፃፀም ማስመዝገብ እንደተቻለ ነው ያመለከቱት።

ከዕቅድ በላይ ማሳካት የተቻለው የአካባቢው ሰላም እየተሻሻለ በመምጣቱና የፖለቲካ አመራሩ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ መሆኑንም አስረድተዋል።

የሥራ ዕድሉ የተፈጠረው በከተማ ግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በብረታ ብረት፣ በአገልግሎትና በሌሎች ዕድገት ተኮር ዘርፎች መሆኑንም አብራርተዋል።

ለሥራ ዕድል ተጠቃሚ ወጣቶች የብድር፣ የመሥሪያና የመሸጫ ቦታ (ሼድ) እንዲሁም የገበያ ትስስር ድጋፍ መደረጉንም አብራርተዋል።

የስራ እድሉ ተጠቃሚ የሆነች የወልድያ ከተማ ነዋሪ ወጣት እመቤት ደምሴ፤ በተደረገላት ድጋፍ በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ በመሰማራት ተጠቃሚ መሆኗን ገልጻለች።

አትክልትና ፍራፍሬ ከመሸጥ ጎን ለጎን እንጀራ በመጋገርና በማቅረብ ጥሩ ገቢ እያገኘች መሆኑንና ሥራዋን ለማስፋት ተግታ እየሠራች እንደምትገኝ ተናግራለች።

ሌላዋ ወጣት ሸዋዬ ኃይሉ በበኩሏ፤ በተሰጣት የሥልጠና ድጋፍ የወረቀት ቦርሳ በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆኗን ገልጻለች።

ከጓደኞቿ ጋር በመደራጀት የጀመረችው ሥራ  በየወሩ እስከ 50 ሺህ ብር ገቢ እያስገኘላቸው መሆኑን አስረድታለች።

በ2019 በጀት ዓመት ለ11 ሺህ 923 ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወደ ሥራ መገባቱን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም