ቀጥታ፡

የመደመር እይታ

በጋራ ትርክት ግንባታ የመደመር መንግሥት ዕሳቤ ምንድነው ?

የፖለቲካችን አንዱና ዋነኛው ክፍተት ከመታገያ አጀንዳችን ጋር የተያያዘ ነው። የጋራ አጀንዳን በመፍጠር አጠቃላይ ሕዝቡን አስተባብሮ በመምራት ረገድ ክፍተት አለበት። ማንነት ላይ የሚያተኩር፣ ከትልቅ አሰባሳቢ ጉዳይ ይልቅ ለልዩነት ቦታን የሚሰጥና አለመግባባት የሰፈነበት ነው። በዚህ የተነሣ ለግጭትና ለፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ነው። በሁለት ጽንፍ ማንነቶችና በአክራሪ ብሔርተኝነት የተወጠረው ፖለቲካችን፣ አቀራራቢ ጉዳዮችን ከፖለቲካ ሜዳው ያሸሸ ነው።

በመጠፋፋት ላይ የተመሠረተው የሁለቱ ጫፍ ፖለቲካ፣ በሐሳብ ገበያው እኩል ቀርቦ የመወዳደር ፍላጎት አይታይበትም። ከዚህም በላይ ይህ በማንነት ላይ የተመሠረተው ፖለቲካ፣ ሌላ ተጨማሪ አማራጭን ይዞ በመምጣት ረገድ ክፍተት አለበት። ፖለቲካችን ከአለመረጋጋት ወጥቶ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል እንዲሆን፣ አግላይ ከሆነ የማንነት ፖለቲካ መውጣት ይገባዋል። አሰባሳቢ በሆኑ የጋራ አጀንዳዎችና ዕሴቶች ላይ መመሥረት አለበት። ፖለቲካችን የአማራጭ ሐሳቦች እጥረት አለበት ብለናል። ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ዋልታ ረገጥ ማንነት ላይ የተመሠረተም ነው፡፡


 

ፖለቲካችን ሁሉን ሊያቀራርብ በሚችል አማራጭ ትርክት እጥረት በሁለቱ ዋልታ ረገጥ ትርክቶች ሽኩቻ ይናጥ ነበረ። ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማረጋገጥና የጋራ ግብን አንግበን በጋራ ጥረት ወደ ብልጽግና ለማምራት፣ በጽንፍና ጽንፍ ያሉ ትርክቶችን ሊያስታርቅ የሚችል ሦስተኛ አማራጭ ትርክት ያስፈልጋል፡፡

ሐሳብ በፖለቲካ ውስጥ የፍላጎት መግለጫና እነዚህን ፍላጎቶች ማሳካት የሚቻልበትን መንገድ የሚተነትን ነው። መደመር ከአክራሪ ማንነቶች በመውጣት በሐሳብ ላይ የቆመ ፖለቲካን ይከተላል። መደመር የሰው ልጆችን ፍላጎቶች ማለትም የሀብት፣ የክብርና የነጻነት ፍላጎቶችን መሠረት ያደረገ ነው። እነዚህን ለማሟላት ደግሞ የራሱን አማራጭ ይዞ ቀርቧል። ብልጽግና የእነዚህ ሰብአዊ ፍላጎቶች መሟላት ውጤት ነው፡፡

የብሔራዊነት ትርክት በነጻነት፣ በእኩልነትና በወንድማማችነት/ እኅትማማችነት ላይ የተመሠረተ ነው። አቀራራቢ በሆነ ታሪክ ላይ ይገነባል። የትናንትን ብቻ ሳይሆን የዛሬ አብሮነትንና የነገ የጋራ ዕጣ ፈንታችንን የሚያመለክት ነው፡፡

ወደ ሐሳብ ገበያ በምናደርገው ጉዞ፣ ለፖለቲካ ገበያ በር የሚከፍቱ ያለፉ ስብራቶቻችንን መጠገንና መሻገር ያስፈልገናል። ለሐሳብ ገበያ መሠረትን ለመጣልና ስብራቶችን ለመጠገን፣ የሚያስችል ብሔራዊ መግባባትን የሚያመጣ ምክክር አስፈላጊ ነው።

ኅብረ ብሔራዊ አንድነትና የተረጋጋ ፖለቲካ ብልጽግናን ለማረጋገጥ መደላድል ነው። ልዩነትን በአግባቡ አለማቻቻልና መከፋፈል ብልጽግናን ለማምጣት ደንቃራ ነው። ምክንያቱም በትብብርና በውድድር መካከል ሚዛን ከመጠበቅ ይልቅ ያልተገባ ሽኩቻን ይፈጥራል። ምክንያቱም ሕዝብን በአንድ ላይ አስተባብሮ ወደ አንድ የብልጽግና ዓላማ ለመምራት አዳጋች ይሆንበታል። የፖለቲካ ኃይሎች፣ የተለያዩ ማንነቶች እንዲሁም በአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ለአንድ ከፍ ላለ ዓላማ ከመቆም ይልቅ፣ ለአነስተኛና ለአንጻራዊ ጥቅም ፉክክር ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ኃይል ይበትናል።


 

በተጨማሪም፣ ልዩነትን የሚፈጥረው ሽኩቻ ትብብርን ከማጥፋት ባሻገር ያልተረጋጋ ፖለቲካዊ ሁኔታና የሰላም መደፍረስ ይፈጥራል። በመሆኑም የመንግሥት ትኩረት፣ ዐቅምና ሀብት እንዲበታተን በማድረግና ፍጥነትን በመቀነስ፣ ብልጽግና ሊረጋገጥ የሚችልበት ጊዜ እንዲራዘም ያደርጋል።

ብሔራዊ መግባባት የሀገራችን ለውጥ ማነቆዎች የሆኑ ጉዳዮችን የምንፈታበት መንገድ ነው። የረጅም ጊዜ ችግሮቻችንንና ስብራቶቻችንን በመጠገን በአንድ ላይ ወደፊት የምንሻገርበት መንገድ ነው፡፡ በፖለቲካ ወደፊት ሳይሻገሩ በኢኮኖሚ ሙሉ ለሙሉ ወደፊት መሻገር የማይታሰብ ነው፡፡

ሀገራዊ ምክክር፣ በአንድ በኩል አንድነትና ኅብረትን በማጠናከር፣ ልሂቃንና ሕዝብ ለአንድ ከፍ ላለ ዓላማ በአንድ ላይ እንዲቆሙ ያደርጋል። በዚህም ጥረቶች ሁሉ በአንድ አቅጣጫ እንዲፈሱ ያደርጋል። በሌላ በኩል ፖለቲካዊ መረጋጋትና ሰላምን በመፍጠር የመንግሥት ትኩረት፣ ሀብትና ጊዜ ሳይበታተን ብልጽግናን ለማረጋገጥ ብቻ እንዲውል ያደርጋል።

የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ከገጽ 402 - 403

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም