የህዳሴ ግድብ ለሱዳን አዲስ የኢኮኖሚ እድል የሚፈጥርና የቀጣናዊ ትስስር መንገድ የሚከፍት ነው-ዓለም አቀፍ የውሃ ኤክስፐርት ፕሮፌሰር ሰይፍ አል-ዲን ሀማድ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ ለሱዳን አዲስ የኢኮኖሚ እድል የሚፈጥርና የቀጣናዊ ትስስር መንገድ የሚከፍት ነው-ዓለም አቀፍ የውሃ ኤክስፐርት ፕሮፌሰር ሰይፍ አል-ዲን ሀማድ
አዲስ አበባ፤ነሐሴ 13/2018 (ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለሱዳን በርካታ የኢኮኖሚና የልማት እድሎችን የሚያስገኝና የቀጣናዊ ትስስር መንገድን ይበልጥ የሚያሰፋ መሆኑን የቀድሞው የሱዳን የውሃ ሀብት ሚኒስትርና ዓለም አቀፍ የውሃ ኤክስፐርት ፕሮፌሰር ሰይፍ አል-ዲን ሀማድ ገለጹ።
ፕሮፌሰር ሰይፍ አል-ዲን ሀማድ ከአል-ኒላይን የዜና ቻናል ''ሙቅረን አል-ኒላይን'' ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ፤ በወንዝ ላይ በደረጃ (Cascade System) የሚገነቡ ግድቦች የተቀናጀና ዘመናዊ አስተዳደር ከተከተሉ፣የወንዙን የተፈጥሮ ፍሰት በማስተካከልና በማረጋጋት ለተፋሰሱ ሀገራት የጋራ ጥቅም የሚሰጡ እንጂ በምንም አይነት መልኩ ስጋት ሊሆኑ እንደማይችሉ አስረድተዋል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የዓባይ ወንዝ በክረምት ወቅት ብቻ በከፍተኛ መጠን ይፈስ የነበረበትን ሁኔታ በመቀየር፣ዓመቱን ሙሉ የተስተካከለና የተመጣጠነ የውሃ ፍሰት እንዲኖር እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ይህም ሁኔታ ለሱዳን በርካታ የኢኮኖሚና የልማት እድሎችን ይዞ እንደሚመጣ አንስተዋል።
ከእነዚህ እድሎች መካከል አንዱ የኤሌክትሪክ ማመንጨት አቅምን ማሳደግ ሲሆን፣ የተስተካከለው የውሃ ፍሰት እንደ ሮዛሪስ እና ሴናር ያሉ የሱዳን ግድቦች ያለ ተጨማሪ ወጪና ህዝብ መፈናቀል ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጩ የሚያስችላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የወንዙ ውሃ ከፍ ማለቱ የሱዳን አባወራዎችና አምራቾች ለግብርና መስኖ ይጠቀሙበት የነበረውን የፓምፕ ወጪ ከ30 እስከ 50 በመቶ ያህል እንደሚቀንስ አስረድተዋል።
በተጨማሪም የተስተካከለው የውሃ ፍሰት በሱዳን የውሃ ላይ ትራንስፖርትን እንደገና እንዲያሰራራ ትልቅ እድል እንደሚፈጥር ፕሮፌሰር ሀማድ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፣ የሕዳሴው ግድብ ይፈርሳል ወይም የጎርፍ አደጋ ያመጣል በሚል የሚነሱ ስጋቶችን ፕሮፌሰር ሀማድ በሳይንሳዊ ማስረጃ ውድቅ አድርገውታል።
ግድቡ ከምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ የመሬት መንቀጥቀጥ ቀጠና 600 ኪሎ ሜትር ያህል የራቀ ከመሆኑም በላይ፣ በካሬ ሜትር እስከ 10 ሺህ ቶን መሸከም በሚችል ጠንካራ የግራናይት ድንጋይ ላይ የተገነባ በመሆኑ ምንም ዓይነት የመዋቅር አደጋ የለበትም ብለዋል።
እንደ የቀድሞው የሱዳን የውሃ ሀብት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ሰይፍ አል-ዲን ሀማድ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባቸው አዳዲስ ግድቦች የውሃ አሞላልን አስመልክቶ ቅድመ ስምምነት ላይ ከተደረሰባቸው በሱዳን ላይ ምንም ዓይነት ስጋት አያመጡም።
ፕሮፌሰር ሀማድ ሱዳን ከተሳሳቱ ስጋቶችና እርግጠኛ ካልሆኑ ሀሳቦች በመውጣት፣የሕዳሴ ግድብ የፈጠረው አዲስ የውሃ እውነታ ጋር የሚጣጣም ብሔራዊ የውሃ ሀብት ስትራቴጂ ማዘጋጀት እንዳለባት አሳስበዋል።
ለዚህም በሀገሪቱ መሪ የሚመራ ብሔራዊ የውሃ ሀብት ምክር ቤት ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል የተቀናጀ እቅድ ማውጣት እንዳለበት ጠቁመዋል።