ቀጥታ፡

በይርጋዓለም ከተማ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር የዶሮ አርቢዎችን ኢኮኖሚያዊ አቅምን እያሳደገ ነው

ይርጋለም፤ ነሀሴ 13/2018 (ኢዜአ)፡-በይርጋዓለም ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩ ማህበራት ከእንቁላል ምርታቸው ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እያሳደጉ መምጣታቸውን ገለጹ።

በሲዳማ ክልል ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ይርጋዓለም ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ማህበራት እንደገለጹት፣ የተሰማሩበት የዶሮ እርባታ ሥራ የእንቁላል ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እያሳደገው ነው። 

ከእንቁላል ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው እያደገ መምጣቱንም ለኢዜአ ገልጸዋል።


 

‎በከተማው የጌዶሴይ ዶሮ እርባታ ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ከተማ ካቢሶ ሥራውን በ1 ሺህ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንደጀመሩ አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ያሏቸው የዶሮዎች ቁጥር 4 ሺህ መድረሱን ተናግረዋል። 

ከእነዚህም በቀን ከ3 ሺህ 700 በላይ እንቁላል እንደሚሰበስቡና ከሽያጩም የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናችውን አስረድተዋል።


 

ከእንቁላል ምርት ባለፈ የአንድ ቀን ጫጩቶችን በማስመጣትና አሳድገው በ48 ቀናቸው ለተጠቃሚዎች በማስረከብ ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከመንግስት የመስሪያ ቦታ፣ የስልጠናና ሌሎች ድጋፎችን እያገኙ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።


 

የደረሰና ቤተሰቡ የዶሮ እርባታ ማህበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ደረሰ አሰፋ በበኩላቸው "የዶሮ እርባታ ሥራ አስፈላጊ መኖና ሕክምናን ከማሟላት ባለፈ በጥንቃቄ መስራት ከተቻለ ትርፋማ ያደርጋል" ብለዋል።

በአንድ ሺህ የእንቁላል ጣይ ዶሮዎች የጀመሩትን ሥራ አስፋፍተው በአሁኑ ወቅት ከ10ሺህ በላይ ዶሮዎች እንዳሏቸው ገልፀዋል፡፡

በቀን ከ9 ሺህ በላይ እንቁላል ለገበያ በማቅረብ ጥሩ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ደረሰ፣ በስራቸው ለሌሎቸም  የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ነው የተናገሩት

ከመንግስት ነጻ የዶሮ ክትባቶችን ጨምሮ የሙያና የተለያየ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡


 

የሲዳማ ክልል እንስሳት ሀብት ልማት ቢሮ ምክትልና የዝርያ ማሻሻልና መኖ ልማት ዘርፍ ኃላፊ አደገ አለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው በክልሉ በሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የዶሮ ልማት ሥራ ትልቅ እመርታ ማሳየቱን ገልጸዋል፡፡

የዶሮ ሀብት ልማት በየቤታቸው የተወሰኑ ዶሮዎችን የሚያረቡ አርሶ አደሮች፣ በማህበር ተደራጅተው የሚሰሩ ዜጎችን እንዲሁም በግል የሚያለሙ ባለሀብቶችን ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።

በዘርፉ ለተሰማሩ ማህበራት እና ዶሮ ፈላጊዎች የዶሮ አቅርቦት፣ የሙያ እገዛና ሌሎች የድጋፍና ክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ኃላፊው አደገ (ዶ/ር) ጠቁመዋል፡፡

እንደእሳቸው ገለጻ ከአምስት ዓመት በፊት በክልሉ በዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በታች የነበረውን የዶሮ ሥርጭት በአሁኑ ወቅት 20 ሚሊዮን ለማድረስ ተችሏል።

በተያዘው 2019 በጀት ዓመትም 24 ሚሊዮን ዶሮዎችን ለማሰራጨት ማታቀዱን ጠቁመዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም