ቀጥታ፡

ቡሄ እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ምስረታ ታሪካዊ ቁርኝት

 በሙሴ መለሰ
 
ዛሬ ነሐሴ 13 ቀን የቡሄ በዓል በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ባለበት በዚህ ዕለት፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ አጀማመሩንና ምስረታውን ከዚህ  በዓል ጋር ያለውን የጠበቀ ትስስር ወደ ኋላ መለስ ብሎ የሚታወስበት ነው።
 
የክለቡ ምስረታና የቡሄ በዓል (የሆያ ሆዬ ጨዋታ) ቀጥተኛና የማይነጠል ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው ሲሆን፣ ክለቡ በመስረታው  ወቅት የነበረበትን የፋይናንስ እጥረት ቀርፎ የመጀመሪያውን ማሊያ ለመግዛት የበቃው በዚህ ዕለት በተሰበሰበ የሙልሙል ዳቦ ሽያጭ ነበር።
 
የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ቡድን መጀመሪያ ሲጠነሰስ በጆርጅ ዱካስና በአየለ አትናሽ አማካኝነት የነበረ ቢሆንም፣ ክለቡን በይፋ አደራጅቶ ለማቋቋም ግን የግድ የፋይናንስ አቅም ወይም ገንዘብ ያስፈልግ ነበር።
 
ሆኖም ግን በሃገር ፍቅር ስሜት የተነሱት  ዘጠኙ  ወጣቶች ማለትም አየለ አትናሽ፣ ጆርጅ ዱካስ፣ ዮሐንስ ጥላሁን፣ ገብረመድህን ተፈሪ፣ ተፈራ ገብረእግዚአብሔር፣ ዓለማየሁ እጅጉ፣ መኮንን ደምሴ፣ አስፋው ያዕቆብ እና ክልቱ አያኖ ክለቡን በሚመሰርቱበት ወቅት ቤሳ ቤስቲን እንኳ ኪሳቸው ውስጥ ስላልነበራቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ተሰብስበው በሰፊው ተወያዩ።
 
በዚህ የውይይት ወቅት ነው ገንዘብ ለማግኘትና የክለቡን መመስረት እውን ለማድረግ የቡሄ ቀን እጅግ መልካምና ትልቅ አጋጣሚ መሆኑን የተረዱት።



 
ዘጠኙ ወጣቶች በአንድ ድምፅ ተስማምተው በታሪካዊው  የቡሄ ዕለት ማለትም ነሐሴ 13 ቀን 1927 ዓ.ም. በጋራ በመሆን ቡሄ ጨፍረው (ሆያ ሆዬ ብለው) በሚያገኙት ማናቸውም ነገር የክለቡን የመጀመሪያ ማሊያ ለመግዛት ቁርጥ የሆነ ውሳኔ ላይ ደረሱ።
 
በዚያን ጊዜ የነበረው የባህል ልማድ አሁን ካለው የተለየ በመሆኑ፣ ቡሄ ሲጨፈር የሚሰጠው ጥሬ ገንዘብ ሳይሆን ሙልሙል ዳቦ ነበር።
 
በመሆኑም ዘጠኙ ተጫዋቾችና መስራቾች ቀደም ሲል ከሚጨፍሩበትና ለምደውት ከነበረው አካባቢ ራቅ ብለው በመንቀሳቀስ በየቤቱ በር እያንኳኩ በደመቀ ሁኔታ ጨፈሩ፤ በዚህም ጥረታቸው በርካታ ቁጥር ያለው የሙልሙል ዳቦ በአንድነት ማሰባሰብ ቻሉ ታሪካዊውን ስራ ሰሩ።
 
ይሁን እንጂ የተሰበሰበውን ይህንን በርካታ ዳቦ ወደ ጥሬ ገንዘብ ለመቀየር አዲስ አበባ ውስጥ ወደሚገኘው ሰራተኛ ሰፈር ለሚገኙ ወዛደሮች ለመሸጥ ዳቦውን በከረጢት ይዘው ጉዟቸውን ጀመሩ።
 
በዚህ የጉዞ መስመር ላይ ሳሉ ግን ያልተጠበቀ ፈተና ገጠማቸው፤ በመንገድ ላይ ያገኟቸው “ዱርዬዎች” ከተሰበሰበው ዳቦ ላይ የተወሰነውን ነጠቋቸው።
 
ወጣቶቹ ተስፋ ሳይቆርጡ ጉዟቸውን በመቀጠል የተረፈውን ዳቦ ለሰራተኛ ሰፈሩ ወዛደሮች በመሸጥ ማሊያ መግዣ የሚሆን ጥሬ ገንዘብ በእጃቸው አስገቡ።

ከዳቦው ሽያጭ የተገኘችው ጠቅላላ የገንዘብ መጠን በወቅቱ መገበያያ በትክክል ሁለት ጠገራ ብር ነበረች።

የክለባችው የመጀመሪያ መለያ ቡናና ነጭ ነበር። ቡናና ነጭ መሊያን የገዙት ግን ፈልገው አልነበረም በቂ ገንዘብ ስላልነበራቸው በሁለት ጠገራ ብር ከፒያሳ «ግሪካዊ አውግስታስ ዱስ» ከተባለ ሱቅ በርካሽ ስላገኙት ነበር።



 
ይህ በቡሄ ዕለት የተጀመረው ታሪካዊ የማሊያ ግዢ በኋላ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ በታህሣሥ ወር 1928 ዓ.ም. በይፋ ተመሠረተ።  ክለቡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለብ በመሆን ታሪካዊ ማዕረግንና ቀዳሚነትን ተቀዳጀ።
 
በ1928 ዓ.ም. በይፋ የተመሰረተው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በታሪኩ የመጀመሪያውን የሜዳ ጨዋታ ያደረገው ከ"አራራት አርመን" ቡድን ጋር ነበር። በዚሁ ታሪካዊ የመጀመሪያ ጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚውን 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል።
 
በዕለቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጠንካራ ተፎካካሪ ከነበረው የ"አራራት አርመን" ቡድን ጋር ለመጫወት ወደ ሜዳ ሲያመራ፣ አስቀድመው ከተመረጡትና ቡድኑን ካደራጁት ተጫዋቾች መካከል አንዱ ባልታወቀ ምክንያት ሳይመጣ ቀረ።
 
በዚህ ድንገተኛ መቅረት ምክንያት ቡድኑ በሰው ጎደሎ ለመጫወት በተገደደበት ወሳኝ ሰዓት፣ መስራቾቹ በሜዳው አቅራቢያ መንገድ ላይ ሲጫወት ያገኙትን አንድ ታዳጊ ወጣት ተመለከቱ።
 
ይህ ታዳጊ በወቅቱ ገና የ14 ዓመት ዕድሜ የነበረውና በኋላ ላይ የኢትዮጵያ ስፖርት ባልደረባ የሆነው ይድነቃቸው ተሰማ ነበር። ወጣቶቹም ያለ ምንም ቅድመ ዝግጅት ቡድኑን እንዲሞላ ድንገት ጋበዙት፤ እርሱም የቀረበለትን ጥሪ በደስታ ተቀብሎ በአጋጣሚ ወደ ሜዳ ገባ።
 
ያለ ምንም ልምምድና ዝግጅት በድንገት የተሰለፈው ይድነቃቸው ተሰማ፣ በሜዳ ላይ ያሳየው አስደናቂ ችሎታና ቅልጥፍና ሁሉንም ያስገረመ ነበር።
 
ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ታሪካዊ ጨዋታ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ፣ ለክለቡ የመጀመሪያውን ድል ያስገኙትን ሁለቱንም ታሪካዊ የማሸነፊያ ግቦች ከመረብ ያሳረፈው ይኸው መንገድ ላይ ተገኝቶ በድንገት የተሰለፈው ታዳጊ ይድነቃቸው ነበር።
 
ይህ ብቃት ገና በታዳጊነቱ በክለቡ ውስጥ ያለውን የማይተካ ቦታ ከማረጋገጡም በላይ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን የድል ጉዞ በደመቀ ሁኔታ እንዲጀመር አድርጓል።
 
ቡሄ በዓል እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ ያላቸው ታሪካዊ ቁርኝት የክለቡን ጥልቅ ህዝባዊና ባህላዊ መሰረት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ህያው ምስክር ነው።
 
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቀዳሚ ፋና ወጊ የሆነው ይህ ታላቅ ክለብ፣ በታሪካዊቷ የነሐሴ 13 ቀን የቡሄ ዕለት የመስራቾቹ የ"ሆያ ሆዬ" ጨዋታና ከተሰበሰበው ሙልሙል ዳቦ ሽያጭ ባገኟት ሁለት ጠገራ ብር የመጀመሪያውን ቡኒና ነጭ ማሊያ መግዛቱ፣ ክለቡ ከህዝብ ማህፀን የወጣ የህዝብ ሀብት መሆኑን ያረጋግጣል።



 
ይህ ከባህልና ከትውፊት ጋር የተቆራኘ አስደናቂ አጀማመር፣ ከጊዜ በኋላ በ1928 ዓ.ም. ለይፋዊ ምስረታው በር ከፋች ከመሆኑም በላይ፣ በታሪካዊው የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ እንደ ይድነቃቸው ተሰማ ያሉ የአፍሪካ እግር ኳስ ታላላቅ መሪዎችና ድንቅ ተሰጥኦዎች እንዲፈጠሩ መሰረት የጣለ የኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም