ቀጥታ፡

የግብጽ እኩይ ሴራ የማይገታው የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት መብት

ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገበች የምትገኘው እና የቀጣናው የጂኦ-ፖለቲካዊ መረጋጋት ዋና መሠረት ነች።

የኢትዮጵያ፣ የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ የፖለቲካ ፍላጎት ሳይሆን ሀገራዊ ሕልውናንና ደህንነትን  የማረጋገጥ፣ የልማትና ብልጽግናን ዕውን የማድረግ የትውልድ ጥያቄ ነው። 
 
ትልቅ አቅም ያላት ኢትዮጵያ በመልክዐ-ምድራዊ እስር ውስጥ እንድትቀር የሚደረገው ተፈጥሯዊና ታሪካዊ ፍትሕን የሚቃረን አካሄድን ለማረም ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት የነበራት የባህር በር ባለቤትነት እና የማሪታይም መብት በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየሰራች ነው።
 
ይህ የኢትዮጵያ ፍትሐዊና የማይቀረው የሕልውና ጥያቄ በዓለም አቀፉ የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS) የተረጋገጠ እና በጋራ ተጠቃሚነት (Win-Win) መርሕ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም፣ የግብጽ ፖሊሲ አውጪዎች ግን ይህንን የሕልውና ጥያቄ ለማክሸፍ የሴራ እና የከበባ ስትራቴጂያቸውን ለማስፈጸም እየሰሩ ይገኛሉ።
 
የግብጽ ሴራ በዋናነት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ ለወደብ ኪራይ እንድታወጣ በማስገደድ፣ ለትምህርት፣ ለጤና እና ለልማት የሚወጣው ካፒታል እንዲሟጠጥ በማድረግ የሀገሪቱን የኢንዱስትሪያላይዜሽንና የልማት ዕድገት ለማቀጨጭ ያለመ የኢኮኖሚ ዘመቻ ነው።
 
በተጨማሪም ግብጽ የቀይ ባሕርን ማሪታይም ቀጣና “የባሕር ዳርቻ ሀገራት ብቻ (Littoral States) ይዞታ" አድርጋ በመሳል፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊና ሕጋዊ የመጠቀም መብት በመካድ ከማንኛውም የቀይ ባሕር የደህንነትና የኢኮኖሚ ስብስብ እንድትገለል እየሰራች ትገኛለች።
 
ግብጽ ከኢትዮጵያ ጎረቤት ሀገራት ጋር የምታደርጋቸው ወታደራዊ ስምምነቶች በሰሜንና በምሥራቅ ድንበሮች አካባቢ አዲስ የደህንነት ስጋት በመፍጠር፣ ኢትዮጵያ ሀብቷንና ትኩረቷን ወደ የብስ ጥበቃ እንድታዞርና ለባህር ኃይል ግንባታ የምታውለውን አቅም እንድታበታትን የታለመ የከበባ ስልትም ነው።
 
በዓለም አቀፍ የፋይናንስና የኢንቨስትመንት ተቋማት ዘንድ የምታደርገው የዲፕሎማሲ ጫና፣ ኢትዮጵያ ለወደብ እና ለትራንስፖርት ኮሪደሮች ልማት የሚሆን የውጭ ኢንቨስትመንት እንዳታገኝ እና የቀይ ባሕር አካባቢ የስጋት ቀጠና ተደርጎ እንዲቆጠር በማድረግ ኢንቨስተሮች እንዲሸሹ በማድረግ ላይ ናት።
 
በጎረቤት ሀገራት ዘንድ የጥርጣሬ እና የስጋት ግንብ በመገንባት፣ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የምታደርጋቸው ፍትሐዊና የጋራ ዕድገትን ያለሙ የወደብ ስምምነቶች የሉዓላዊነት መጣስ ተደርገው እንዲቆጠሩ የማስፈራራትና የሐሰት ትረካና ዘመቻ ታካሂዳለች።
 
ግብጽ የአፍሪካ ህብረት እና የኢጋድ አባል ሀገራት በኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ላይ አንድ ወጥ አቋም እንዳይዙ ለማድረግ ድርጅቶቹን የፖለቲካ ፍልሚያ መድረክ በማድረግ የቀጣናውን ተቋማዊ ትብብር የማደናቀፍ ተግባር እያከናወነች ይገኛል።
 
የግብጽ ሚዲያዎች የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ የ130 ሚሊዮን ሕዝብ የረጅም ጊዜ ሕልውና እና የትውልድ ጥያቄ መሆኑ እየታወቀ ጠባብ የፖለቲካ አጀንዳ በማስመሰል ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲይዝ የማድረግ ስራ ላይ ተጠምደዋል።
 
ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉራዊ የነፃ ንግድ ቀጣና (AfCFTA) ውስጥ የምታደርገውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ፣ የወደብ ትራንዚት ወጪዋ ከፍተኛ ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ ምርቶቿ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪነት ላይ ጫና ለመፍጠር ትሰራለች።
 
የግብጽ የመጨረሻ ግብ ኢትዮጵያን ለዘለቄታው የመልክዐ-ምድር እስረኛ አድርጎ በማስቀረት፣ በምሥራቅ አፍሪካ የሚኖራትን ጂኦ-ፖለቲካዊና የኢኮኖሚ የበላይነት መግታት  ነው።
 
ሆኖም የግብጽ ሴራ የኢትዮጵያን የልማት መንገድ ሊያስቆመው አይችልም። ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በሕዝቦቿ የማይበገር ጽናትና ቁርጠኝነት እውን እንደሆነ ሁሉ፤ በቀይ ባህር ላይ ህጋዊና ፍትሃዊ መብትን የማረጋገጥ ጉዞም የቀጣናውን የታሪክ ሂደት የሚቀይር የማይቀለበስ ብሔራዊ የህልውና ጉዳይ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም