ቀጥታ፡

ቡሄ የትውልድ ወጋገን፤ የማኅበራዊ ትስስር አምድ

ቡሄ በወርሃ ነሐሴ በ13ኛው ቀን ህፃናት ሆያ…. ሆዬ….! ሆ…. በሚል ዜማና ጅራፍ እያጮሁ የሚያከብሩት፤ እናቶች ለህፃናቱ ሙል ሙል ዳቦ በመስጠት እንኳን አደረሳችሁ እያሉ በድምቀት የሚያከብሩት በዓል ነው። 

ቡሄ ትርጓሜውም ብርሃን፣ብራ፣ ወጋግን ማለት ሲሆን ከጨለማ ወደ ብርሃን የመሸጋገሪያ የተስፋ ምልክት ነው።  

በሀይማኖታዊ አንድምታው በዓሉ የኢየሱስ ክርስቶስ መለኮታዊ ብርሃን በደብረ ታቦር ተራራ ላይ መገለጡ የሚታሰብበት ነው፤ በዚህም ደብረ ታቦር ይባላል፡፡

የክረምቱ ጭጋግ ተገፎ የብርሃን ወጋገን የሚታይበት ሕፃናትና ወጣቶች በየቤቱ እየዞሩ «ሆያ ሆዬ» በማለት በረከትና ምርቃት የሚያፍሱበት የደስታና የፍቅር መግለጫ ነው።

ህፃናትና ወጣቶች በየዕድሜያቸው ጅራፍ እያጮሁ በሕብረ ዝማሬዎች እየደመቁ በአብሮነት እና በደስታ የሚያከብሩት ትውፊታዊ በዓል ነው ቡሄ።

የወጣቶችን ጉርብትና እና ማኅበራዊ ትስስር የሚያጎለብት እሴት ነው፤ በአከባበሩ ወቅት የሚንጸባረቀው የመረዳዳትና ያለውን የመካፈል ባህል ፋይዳውን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማሸጋገር ያስችላል።

የቡሄ በዓል ባህላዊ እሴቶችን በመጠበቅ፣ ትውልድን በማቀራረብ እና ማኅበራዊ ትስስርን ይበልጥ በሚያጠናክር ተምሳሌትነቱ እልፍ ነው።

በአዲስ አበባ ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናት ተመራማሪ መምህር መክብብ ገብረማሪያም ለኢዜአ እንዳሉት፤ የቡሄ በዓል የብርሃን ዘመን መምጣቱን የተስፋ ጎህ መቅደዱን ማብሰሪያ ነው፡፡

ቡሄ ከጨለማ ወደ ብርሃን ሽግግር መምጣቱን የሚያበስር በታዳጊዎች የሚዘከር የፍቅር፣ የአንድነትና የበረከት መገለጫና ተስፋ መሆኑን ያነሳሉ፡፡

ታዳጊዎችና ወጣቶች በበዓሉ ወቅት የሚያዜሙት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገር የመጣው የ«ሆያ ሆዬ» ሕብረ ዜማ  ለጋራ ትርክት ግንባታ ገንቢ ሚና እንዳለውም ገልጸዋል።

ቡሄ የትውልድ ወጋገን፤ የማኅበራዊ ትስስር አምድ በመሆኑ ማኅበራዊ ትስስርና የጋራ ዕሴቶችን ማጠናከር ያስችላል ብለዋል።


 

ታዳጊው በሱፈቃድ አስሜ ቡሄ ከጓደኞቹ እና ከወዳጅ ዘመዶቹ ጋር ፍቅርንና አብሮነትን ይበልጥ የሚያጠናክርበት የደስታና የተስፋ በዓል መሆኑን ይናገራል፡፡

ቡሄ በየዓመቱ በጉጉት የሚጠብቀውና ቀጣይ ሕይወቱን በአዲስ መንፈስ ለመምራት አቅም የሚፈጥርለት የብሩህ ዘመናትን ማለሚያ መሆኑን ይገልፃል።

ቡሄ ከታላላቆቹ የወረሰው ከእኩዮቹ ጋር በፍቅርና በደስታ የሚያከብረው ነገን በተስፋ የሚያይበት ውብ በዓል እንደሆነ የሚናገረው ደግሞ ታዳጊው በረከት ምናለ ነው፡፡


 

የተጣሉ ጓደኛሞች እርቅ የሚያወርዱበት በዓል በመሆኑ ለትውልድ አንድነት እና አብሮነትን በማስተማር ረገድ ትልቅ ድርሻ አለውም ብሏል።

ወጣት ያብስራ ጸጋዬ በበኩሉ ቡሄ በዓመት አንድ ጊዜ የሚመጣ፤ ተራርቀው ከሚኖሩ የተለያዩ አካባቢ እኩዮቹ ጋር በአንድነት የሚያከብሩት በዓል መሆኑን ይናገራል፡፡


 

ከሁሉም ዓይነት ሕብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ ታዳጊዎች የሚሰባሰቡበት፤ ሕብረ ብሔራዊነትን የሚያጠናክር የጋራ በዓል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ አቶ በኃይሉ ሞገስ ናቸው።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም